በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት የህዝቡን ሃዘን ከባድ ያደረገው በተለይ እንዲያ በክብር ዘብ ታጅበው ሲፈልጉ ሮጥ ሮጥ ብለው፤ በሌላ ቀን ደግሞ በመሪነት ግርማ ረጋ ብለው፣ ሲመላለሱበት በነበረው አውሮፕላን፤ እንዲያ በከፍተኛ ባለስልጣናት አሸኛኘትና አቀባበል ሲደረግላቸው የነበሩ መሪ፤ በዚያው አየር መንገድ ከል በለበሱ ሃዘንተኞች የታጀበ አስከሬናቸው መምጣቱ ይመስለኛል፡፡
እናም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ብዙ ተባለ፡፡ አንዳንዱ “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ምክንያቱ ከጋናው ፕሬዚዳንት ጋር የጨረር ጥቃት ተፈጽሞባቸው ነው፡፡ ሌላ አፍሪካዊ ፕሬዚዳንትም የጥቃቱ ሰለባ ሆነው በሞትና በህይወት መሃል ይገኛሉ” ሲል፤ ሌላው ደግሞ “የለም የዋልድባን ገዳም በመዳፈራቸው መነኮሳቱ መቋሚያቸውን ዘቅዝቀው፤ መስቀላቸውን ከዛፍ ላይ ሰቅለው መሪር ሃዘን ስላዘኑ፤ አምላክ ጸሎታቸውን ሰምቶ የሃይማኖት መሪውንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ቀሰፋቸው” እያለ ወሬውን ሲያጋግል ሰንብቷል፡፡ ያም ሆኖ ሁለቱም ወገኖች ለወሬዎቻቸው “ይህ ነው” የሚሉት ማስረጃ የላቸውም፤ ወይም አላቀረቡም፡፡
በሃዘኑ ሰሞን ሌላ ጉዳዮችም ተስተውለዋል፡፡ ሃዘን በሰላማዊ ሰልፍ የተገለጸበትን ብዙ አካባቢ በቴሌቪዥን አስተውለናል፡፡ እንደሚገባኝ ሰልፍ ለድጋፍ ወይም ለተቃውሞ የሚደረግ መግለጫ ነው፡፡ አለዚያ የቀለጠ መፈክር እያስተጋቡ መሰለፍን ምን አመጣው? “የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገዳይ /እግዚአብሔርን/ እቃወማለሁ” ማለት ነው? ወይስ “ሞታቸውን እደግፋለሁ?” ግልጽ አይደለም፡፡
ህዝቡ እንደየ ባህሉ ሃዘኑን የገለጸበት መንገድ ተገቢም ትክክልም ይመስለኛል፡፡ ድብልቅልቁ የወጣ ሰልፍ ግን ባህላችንም ልምዳችንም አይደለምና ለሃዘን መግለጫ ባናውለው ጥሩ ነበር ባይ ነኝ፡፡
ወቅቱ ለብዙ ወሬ ምቹ ስለነበር በንግዱ አካባቢም ብዙ ተወርቷል፡፡ “የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፎቶ በትላልቅ ሰሌዳዎች እናሰራለን” በማለት ተገቢ ያልሆነ ወጭ እንዲወጣና ብዙው ገንዘብ ወደ ኪሳቸው እንዲገባ ያደረጉ ባለስልጣናት ቁጥር ቀላል አልነበረም እየተባለም ተወርቷል፡፡ በማስረጃ አስደግፎ የሚያቀርብ ባይገኝም፡፡
ጉዳዩ ተፈጽሞ ከሆነ ግን ትልቅ የሞራል ዝቅጠት በመሆኑ በእጅጉ ያሳፍራል፡፡
ባለ ፎቶ ቤቶችም ትንፋሻቸው እስክትወጣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፎቶ በማባዛትና ለቸርቻሪዎች በመቸብቸብ ተወጥረው ሰንብተዋል፡፡ ህዝቡ የመሪውን ፎቶግራፍ የሚገዛው ፍቅሩን ለመግለጽ ነው እንበል፡፡ ግን … የአንድን ሰው ፎቶግራፍ ያለ ባለቤቱ ፈቃድ ወይም የሚመለከተው አካል ሳይፈቅድ በአደባባይ መቸብቸብ በህግ አያስጠይቅ ይሆን?
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ሃዘናቸውን ለመግለጽ በሚኒባሶች ሆድና ጀርባ ታጭቀው “መለስ አልሞተም!” እያሉ የሚጮኹ በርካታ ሰዎችንም ተመልክተናል፡፡
“ሃዘናችንን ስንገልጽ በቦታው ተገኝታችሁ አልቀረጻችሁንም፡፡ ስናለቅስም ሆነ መፈክር ስናሰማ በቴሌቪዥን አላስተላለፋችሁልንም” ብለው የኢቴቪ ባለሙያዎችን የወረፉ ባለስልጣናትና አንዳንድ ሃዘንተኞች እንደነበሩም ሰምተን ገርሞናል፡፡ ለመሆኑ ለቅሶ ቤት የሚኬደው ለመተዛዘን ነው ለመተዛዘብ? ግልጽ አይደለም፡
በቴሌቪዥን ሲተላለፉ ከነበሩት የሃዘን መግለጫዎች አንዳንዶቹ በድፍረትም ሆነ በስህተት ጥሩ ያልሆነ መልዕክት ያዘሉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ጐዳና ተዳዳሪዎች ባካሄዱት የሃዘን መግለጫ ስነ ስርዓት ላይ “አባታችን ስላሉኮ ነው ጐዳና የምንተዳደረው” ብሎ ያለቅስ የነበረን ወጣት በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን አይተናል፡፡
በውጭ ያሉ አንዳንድ ወገኖችም በማህበራዊ ድረ ገጽ የሚያስተላልፉትን መልእክትም በመገረም እያየነው ሰነበትን፡፡ አንዳንዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት በደስታ ሲገልጽ፣ ሌላው ደግሞ አገር ቤት እንዳለው ሁሉ መሪር ሃዘኑን አስተጋብቷል፡፡ በእኔ እምነት ሞትን ለሰው ልጆች ሁሉ የሚመኙ ሰዎች ጤነኛ ናቸው አልልም፡፡ ሃሳብን በሃሳብ መፋለምና ማሸነፍ ሌላ፤ የሰውን አካል ማሸነፍ ሌላ፡
“ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚተካቸው ማን ይሆናል?” የሚለውም ሌላው ዐቢይ አጀንዳ ነበር፡፡ በመሰረቱ ይህ ጉዳይ ሁሉንም ወገን የሚመለከት ስለሆነ አወያይነቱ ተገቢ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በፓርቲውም ሆነ በመንግስት መሪነት ብዙ ጊዜ ስለቆዩ “እሳቸው ከሌሉ ሃገሪቱም የሚመሯቸው ፓርቲዎችም (ኢህአዴግና ህወሃት) ላይኖሩ ይችላሉ” የሚለው ስጋት በአንድ በኩል ትክክል ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ሃያ አንድ አመታት ሁሉ አቶ መለስ የህወሃትንም ሆነ የኢህአዴግን መሪነት ለሌላ ማስተላለፍ አልከጀሉምና ነው፡፡
ይህ ደግሞ አንድም በፓርቲዎች ውስጥ “ለዚህ ኃላፊነት የሚበቃ ሰው የለም” ብለው ያምኑ ነበር፤ ወይም ለስልጣናቸው በእጅጉ ይጠነቀቁለት ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡ ለነገሩ ዜና ዕረፍታቸው ከተነገረ በኋላ በፓርቲው ታላላቅ ባለሥልጣናት ሲነገርላቸው የነበረው ገድል፤ ከእሳቸው በቀር በፓርቲው ውስጥ ምንም ዓይነት ድርሻ የነበረው ሰው እንደሌለ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
አንድን ሰው እንከን - አልባ አድርጐ የሳለው የዚህ ዓይነቱ እጅግ የተጋነነ አገላለጽ፣ ፓርቲውን ከጥርጣሬ ላይ ቢጥለው ላያስደንቅ ይችላል፡፡ ሁሉም ነገር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ የሚያልቅ፣ የሚተነተንና የሚተገበር ከነበረ ንጉሠ ነገስቱን ተክተዋቸው ነበር ማለት ነው፡፡ እግረ መንገዱንም ፓርቲው የአንድ ሰው የግል ሃብት፣ አባላቱም ትዕዛዝ ፈጻሚዎች እንጂ ረብ ያለው ድርሻ አልነበራቸውም ቢባል ስህተት አይመስለኝም፡፡
ሃገሪቱ በአንድ ሰው ሳይሆን በህግ የበላይነት የምትመራ ከነበረ፣ መከላከያውም ሆነ ፖሊሱና ደህንነቱ ለህገ መንግስቱ ታማኞች ከሆኑ ቀጣዩ የሃገራችን ዕጣ የሚያሳስብ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በህገ መንግስቱ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ምክትሉ የእሱን ሥራ ተክቶ የመሥራት ኃላፊነት አለውና ነው፡፡
ትልቁ ችግር ሊሆን የሚችለው በነባር እና ከግንቦት ሃያ በኋላ በተቀላቀሉ ታጋዮች፤ እንዲሁም በመንደርተኝነት መሳሳብ ሲመጣ ነው፡፡
ይህ እጅግ አደገኛ ጉዳይ ነው ባይ ነኝ፡፡ ሃገሪቱንም ሆነ ህዝቡን የሚጐዳው፤ ፓርቲው ከላይ በጠቀስናቸውና በመሰል ጉዳዮች ክፍተት ሲፈጥር ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ፓርቲው በጥቃቅን ሰበብ አስባቦች ካልተዳከመና ውስጣዊ ጥንካሬውን አጽንቶ ከቀጠለ ስጋታችን ሁሉ ስጋት ሆኖ ይቀራል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘውም ሆነ ሆኖለት ማየት የሚፈልገውም ይህን ብቻ ይመስለኛል፡፡ ይህ ከሆነ እንባችን በጉንጫችን ላይ ብቻ ወርዶ የሚቀር ሳይሆን እንደ ራሄል እንባ ከፈጣሪ ፊት ደረሰ ማለት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment