ተበዳሪው ሼክ አል አሙዲ ብድሩን ለመውሰድ ጥያቄ ያቀረቡት ለአፍሪካ ኅብረት ለሚያሠሩት ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ሕንፃ ሊፍት መግዣና መግጠሚያ ነው፡፡ ብድሩም በቀጥታ ሊሰጥ የታቀደው ሊፍቱን ለሚያስመጣው ኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ ለተባለው ሌላኛው የሼክ አል አሙዲ ኩባንያ ሲሆን፣ ንግድ ባንክ ለሊፍቱ ማስመጫ ራሱ ኤልሲ ከፍቶ ኮሚሽን ከማግኘት ይልቅ፣ በኤልሲ ኮሚሽን የሚያገኘውን ገቢ ትቶ በቀጥታ ለኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ ብድሩን ለማስተላለፍ መምረጡ፣ የብድር ክፍል ሠራተኞችን ያስገረመ ጉዳይ እንደሆነ የባንኩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ለሼክ አል አሙዲ ኩባንያዎች 942 ሚሊዮን ብር ብድር መፍቀዱን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ብድሩ የፀደቀው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለሚገነባው የአፍሪካ ኅብረት ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ሕንፃና ለማያ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ ግንባታ ነው፡፡ ለአፍሪካ ኅብረት ሆቴል ሕንፃ ማጠናቀቂያ 850 ሚሊዮን ብር ተፈቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ለከረጢት ፋብሪካው ግንባታ ደግሞ 92 ሚሊዮን ብር ነበር ቦርዱ ያፀደቀው፡፡ ለብድር ማስመለሻ የተያዙት ዋስትናዎች (ኮላተራልስ) እየተገነቡ ያሉት የሆቴል ሕንፃና የከረጢት ፋብሪካዎች ነበሩ፡፡
ሚድሮክ የአፍሪካ ኅብረትን ባለአምስት ኮከብ ሆቴልን ለመገንባት በ1998 ዓ.ም. 90 ሺሕ ሔክታር መሬት መረከቡ ይታወሳል፡፡ ሚድሮክ የወሰደው የአዲስ አበባ አስተዳደር ለአፍሪካ ኅብረት የሰጠውን መሬት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ለሆቴሉ ግንባታ ጨረታ ቢያወጣም ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ግን ፕሮፖዛል በማቅረቡ ጨረታውን ሰርዟል፡፡ ፕሮፖዛሉን በመቀበልም ቦታውን በስሙ ያዛወረለት ሲሆን፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር የሊዝ ቢሮ በወቅቱ ዝውውሩን አፅድቋል፡፡ ባለፈው ዓመት ይህ መሬት ለሴኩዩሪቲና ለፓርኪንግ አገልግሎት አይበቃኝም ያለው ሚድሮክ ተጨማሪ 17 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ አስተዳደሩን ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሆቴሉ ግንባታ በሚድሮክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እየተካሄደ ነው፡፡
በሌላ በኩል በጂቡቲ ወደብ በየጊዜው የሚከማቹ የገቢ ዕቃዎችን በተገቢ ፍጥነትና ጊዜ ለማንሳት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሁለት ሺሕ አዳዲስና ፈጣን የጭነት ከባድ ተሽከርካሪዎች የግል ባለሀብቶች እንዲያስመጡ፣ ለማስመጫ የሚሆናቸውን ብድር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲበደሩና አስፈላጊውን የውጭ ምንዛሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርብ ከአምስት ወራት በፊት ወስነው ነበር፡፡ ነገር ግን ለተሽከርካሪዎቹ መግዣ የሚሆነውን አምስት ቢሊዮን ዶላር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊያቀርብ ባለመቻሉ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እኩሌታውን በውጭ ምንዛሪ ለንግድ ባንክ ለመስጠት ቢስማማም፣ ባጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ዶላሩን ማቅረብ ባለመቻሉ ተሽከርካሪዎቹን ለመግዛት እንዳልተቻለ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊ፣ ባንኩ የነበረው ተቀማጭ ገንዘብ በሰኔ ወር 2004 ዓ.ም. መጨረሻ ከአሥር ቢሊዮን ብር በታች በማሽቆልቆሉ፣ የባንኩን የማበደር አቅም እንዳገደውና የፌዴራልና የክልሎች በጀት በብዛት የሚለቀቅ ከሆነ የተቀማጭ ገንዘቡ ሊያድግ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘንድሮ ለመንግሥት የልማት ሥራዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ብድር ማቅረብ ያለበት ሲሆን፣ በ40/60 ለሚሠሩ የመኖርያ ቤቶች ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ አቅሙን ለማጠናከር ተጨማሪ ቅርንጫፎች በመክፈት ስምንት ቢሊዮን ብር ባለፈው ዓመት ለማሰባሰብ የቻለ ቢሆንም፣ በሽልማትና በሎተሪ አማካይነት ሊያሰባስብ ያቀደው ተቀማጭ ገንዘብ ግን እንደታሰበው እንዳልሆነ የባንኩ ባለሙያዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
Reporter News Paper
No comments:
Post a Comment