“ከእነ ቤተሠቤ እዚህ ለመድረስ ያየሁትን ፈተና ፈጣሪ ያውቀዋል፡፡ ቤተሰቤ ከቁጥር ሳይጐድል ለአገሬ መሬት በቅቻለሁና ከእንግዲህ የፈለገው ይሁን” አሉኝ፤ ከቤኒሻንጉል ክልል ያሶ ወረዳ ተፈናቅለው በፍኖተ ሰላም ድንጋያማ መጠለያ ውስጥ ያገኘኋቸው አዛውንት፡፡ በአማራ ክልል የከሠላ ወረዳ ተወላጅ የኾኑት አዛውንት፤ ኑሮ አልቃና ቢላቸው በ1997 ዓ.ም ሦስት ልጆቻቸውን ከትዳር አጋራቸው ጋር ይዘው፣የትውልድ ቀያቸውን ለቀው የተሻለ ሥራ ይገኝበታል ወደ ተባሉበት ቤንሻንጉል ክልል ያቀናሉ፡፡ ኑሮአቸውንም በቤኒሻንጉል ክልል ካደረጉ በኋላ ተጨማሪ አራት ልጆችን አፍርተው የቤተሠባቸውን ቁጥር ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደርጋሉ፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት ቀን ከሌት እየሠሩም ኑሮአቸውን መምራት ይቀጥላሉ፡፡ ለዓመታት ከኖሩበት መንደር በድንገት እንዲለቁ ሲገደዱ ግራ የተጋቡት አዛውንት የስምንት ልጆች አባት በመኾናቸው ሲፈናቀሉ ከፍተኛ ውጣ ውስጥ ከተታቸው፡፡ በቀላሉ የሚሳካላቸው አልኾነም፡፡
‹‹ ከያሶ ወረዳ ውጡ ተብለን ድብደባና እንግልት ሲደርስብን እንደ ሌሎቹ እመር ብዬ መሸሽ አልኾን አለኝ፡፡ ልጆቼንና ባለቤቴን እንዴት ላድርጋቸው? ከአንድ ቤት ዘጠኝ ሰው የትስ ነው መውደቂያችን? ስል ጭንቀት ገባኝ›› የአዛውንቱ ዐይኖች እንባ አቀረሩ፡፡ አሁን አዛውንቱ ብዙ ስቃይ አልፈው በአማራ ክልል ፍኖተ ሰላም ከተማ ከሌሎች 3500 ተፈናቃዮች ጋር ከእነ ቤተሠባቸው በችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በሚኖሩበት አካባቢ የእርሻ ቦታ ባለማግኘታቸው የተሻለ ሥራ ፍለጋ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ኑሮአቸውን ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያዛወሩ የአማራ ተወላጆች ካለፉት ሦስት ሣምንታት ጀምሮ በወረዳው ባለሥልጣናትና ፖሊሶች ከቀያቸው ተፈናቅለው በምስራቅ ጎጃም በጀቢጠናን ወረዳ ፍኖተ ሰላም ከተማ በሚገኝ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ በደረሰን ጥቆማ መሰረት ወደዚያው አመራን፡፡ ከመጠለያው ወዲህ ከንፈሯ ክው ብሎ ደርቋል በጥቁር መናኛ ሻሽ እራሷን ጠፍንጋ አስራዋለች፡፡
የለበሠችው ቀሚስ ዳር ዳሩ ተተልትሏል፣ የተጫማችው ላስቲክ ጫማ ብዙ ቦታ ተበሣስቷል፡፡ በጠይም መልኳ ላይ ድካምና ተስፋ መቁረጥ ይነበብባታል- በፍኖተ ሰላም ከዳሞት ሆቴል ጀርባ ከአውቶብስ መናህሪያ ዝቅ ብሎ ባለው ‹‹ፍቶተ ሠላም›› ክሊኒክ መግቢያ በር ላይ ያገኘኋት የ27 ዓመቷ ወጣት የአራት ወር ነፍሰ ጡር ናት፡፡ በጉዞዋ በደረሰባት እንግልት በመታመሟ ከመጠለያው ለህክምና ወደ ክሊኒኩ እንደመጣች ነገረችኝ፡፡ “ራሴን ያዞረኛል፣ ሰውነቴን በጠቅላላ ይቆረጥመኛል፣ ያስለኛል፣ በተለይ ሌሊት ሌሊት እንቅልፍ የለኝም” የምትለው ነፍሠ ጡሯ፤ ባደረገችው ምርመራ ደም ማነስ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳጋጠማት ተነግሯታል፡፡ ባለቤቷም የታዘዘላትን መድሀኒት ሊገዛ ሄዷል፡፡ “ቀን ፀሀዩ፤ ማታ ብርዱ በዚያ ላይ ያለ ምንጣፍ ጠጠር ላይ እየተኛሁ ነው ለበሽታ የተጋለጥኩት፡፡ ከዚህ ቦታስ በሕይወት የምገኝ አይመስለኝም” አለች፡፡ ባለቤቷ ተመልሶ ሲመጣ ጨዋታው አላማረውም፡፡
ማንነቴን ጠይቆኝ ከተረዳ በኋላ፤ “እዚህ ያሉ የከተማው አስተዳደሮችና የክልሉ ኃላፊዎች አሁን ያለው ችግር እስኪፈታ ለማንም አትናገሩ ብለውናል” አለኝ፡፡ ‹‹አንዳንድ ጋዜጦች ከመካከላችሁ ያልሆነ መረጃ እየወሠዱና እየጻፉ ጋዜጣ ማሻሻጫ አድርገዋችኋል፤ ስለዚህ ዝም በሉ ተብለናል” የሚል ምላሽ ሠጠኝ፡፡ ችግሩን እንዲነግረኝ ለማግባባት ሞከርኩ፤ “ዋ! ለሠው ቢያወሩት መፍትሄ ካልመጣ ምን መላ አለው እህቴ?” በማለት መልሶ ጠየቀኝ፡፡ በእግራችን እየተጓዝን መጠለያው አካባቢ ደርሰን ነበርና ባለቤቱን ወደመጠለያው አስገብቶ አቧራማው ሜዳ ላይ ተቀምጠን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ገባን፡፡ የ31 ዓመቱ ወጣት አዲስ አበባ ውስጥ ለ12 ዓመታት በሎተሪ አዟሪነት ሠርቷል፡፡ ቤተ መንግሥት አካባቢ በሚገኘው ግቢ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ኢትዮጵያ አንድነት ት/ቤት ጐን ከአራት ጓደኞቹ ጋር ቤት ተከራይቶ ይኖር ነበር ፡፡ “አሥራ ሁለት ዓመት አዲስ አበባ ስኖር ለውጥ አጣሁ፡፡ ስለዚህ አገሬ ገብቼ ሚስት አግብቼ ወገኖቼ እንደሆኑት እሆናለሁ ብዬ ጐጃም ገባሁ” የሚለው ተፈናቃይ፤ አገሩ ከገባም በኋላ ተስፋ የሚሠጥ ነገር አልተመለከተም፡፡ ሆኖም ቤተሠቦቹ ልቡ እንዲረጋ በሚል አስቀድሜ ክሊኒክ በር ላይ ያገኘኋትን ጠይም ቆንጆ ልጅ ዳሩለት፡፡
የሙሽርነት ወጉን በአግባቡ ሳይጨርስ ሚስቱን አሣምኖ ይዟት ቤኒሻንጉል ያሶ ወረዳ ጥቅሻ ቀበሌ እንደገባ አጫወተኝ፡ ይህ የሆነው በ1999 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ ነበር፡፡ ቀበሌዋ እጇን ዘርግታ እንደተቀበለችው ይናገራል፡፡ እንደ ሌሎች ያገሩ ልጆች እርሱም ከጉሙዝ ባለ መሬት ጋር ተስማምቶ ግብርናውን ቀጠለ፡፡ ባለ መሬቱ በሠጠው ቦታ ላይ ጥሩ ቤትም ሠራ፡፡ ህይወት ከአዲሶቹ ሙሽሮች ቤት በፈገግታ ገባች፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት በጥሩ ሁኔታ ከተደላደለ በኋላ ልጅ ለመውለድ ከባለቤቱ ጋር ተመካክሮ ሚስት ፀነሠች፡፡ የአራት ወሩ ፅንስ ግን ዕድለኛ አልኾነም፤ መፈናቀል ተከሠተ፡፡ “አንተ ታመልጣለህ እኔ አቅመ ደካማ ነኝ፤ ከኅብረተሠቡ ጋር ልሣፈርና ልሂድ›› በማለት ባለቤቱ ቀድማው ወደ ፍኖተ ሠላም ትመጣለች፡፡ እርሱ እንዴት የለፋሁበት በቆሎና ሠሊጥ መና ይቀራል በሚል ብቻውን ጫካ ይገባል፡፡ ወደ እህሉ ክምር ሲመጣ፣ ባለ መሬቱ አሠሪው ሌሊቱን ሲወቃ አድሮ በማዳበሪያ ከቶ ያገኘዋል፡፡ “አሠሪዬ መኪና አምጥቶ የራሱ አስመስሎ የኔንም ጫነልኝ፡፡ 40 ኩንታል በቆሎ በ200 ብር ሂሣብ ሸጬ፣ ስንቄን ይዤ ድብደባና እንግልት ከበዛበት ቀበሌ ለማምለጥ ጥሻ ጥሻውን ስመጣ ሊገድሉኝ ለጥቂት አመለጥኩ›› ነበር ያለኝ፡፡
በፍኖተ ሰላም ባከል መንደር ስድስት ወይም በተለምዶ “ቄራ ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለድንጋይ መጥረቢያነት ሲያገለግል የቆየ ኮረት ድንጋይ የፈሰሰበት ሰፊ ሜዳ ለጠራቢዎቹ ፀሐይ መከላከያ በሚል በተሠራው አምስት ቦታ ላይ ተፈናቃዮቹ ሰፍረዋል፡፡ ወደ መጠለያው ስጠጋ ለእርዳታ ሥራ እንደመጣች የገመትኳት ዩናይትድ ኔሽን ‹‹UN›› የሚል ሰሌዳ የለጠፈች ላንድ ክሩዘር መኪና በመጠለያዎቹ ቦታዎች መሐል ለመሐል ቆማለች፡፡ አምስተኛው መጠለያ አካባቢ ሁለትና ሦስት ፖሊሶች ተመለከትኩና መጠለያው እየተጠበቀ እንደኾነ ገምቼ ራሴን ደበቅ አደረኩ፡፡ ግድግዳ አልባ መጠለያ መጠለያዎቹ በወጣቶች፣ በእናቶች፣ በህፃናትና በአዛውንቶች ተሞልተዋል፡፡ አጠቃላይ ቁጥራቸው ወደ 3500 ይገመታል፡፡ ለመኝታ አይደለም ለመቀመጫ በማይመቸው ድንጋያማ ግርግዳ አልባ ባለ ቆርቆሮ ጣሪያ መጠለያ ውስጥ ደቀቅ ያሉትን ጠጣሮች ደልድለው ጎናቸውን አሳርፈዋል፡፡ ጠንከር ያለ አቅም ያላቸው ደግሞ ራቅ ብለው በመሄድ የባህር ዛፍ ቅጠል መልምለው ለማረፊያቸው ጉዝጓዝ አመቻችተው፣ ቢያንስ ካገጠጡት ጠጠሮች ጉርባጤ ራሳቸውን ይከላከላሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉት አብዛኞቹ ግን መሬቱ ላይ ተኝተዋል፡፡ የሸራ ምንጣፍ ያነጠፉ አንዳንድ ሰዎችንም አስተውያለሁ፡፡ የቆርቆሮ ጣሪያ ብቻ ያላቸው ‹‹መጠለያ›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አምስቱ ቦታዎች በመሙላታቸው ሲመሽ ሜዳው ላይ የሚተኛው ተፈናቃይ ቁጥር እንደሚጨምር ነገሩኝ፡፡ መጠለያውን በዐይኔ ቃኘሁት፡፡
አራስ ሕፃናት ያቀፉ እናቶች፤ ልጆቻቸውን ከንፋስና አቧራ ለመከላከል ይታገላሉ፡፡ ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በደረቅ ሜዳ ተሰጥተው ንፋስና ፀሐይ ሲፈራረቅባቸው ማየቱ መንፈስን ይረብሻል፡፡መብራት የሌለውና እና ለዛ ሁሉ ተፈናቃይ ሁለት የውሃ ቧንቧ ብቻ ባለው መጠለያ፤ እናቶች ባዶ የፕላስቲክ ውሃ መያዣዎችን አንጠልጥለው ውሃ ፍለጋ ወደ ከተማው መሀል ይሄዳሉ፡፡ ተፈናቃዮች በውሃ ችግር የተነሳ በከተማዋ መግቢያ ላይ ወደሚኘው “ላህ” የተባለ ወንዝ እየሄዱ ይታጠባሉ፡፡ ጠዋት እና ማምሻውን ከምግብ ዋስትና የሚቀርብላቸው በነፍስ ወከፍ አንድ እንጀራ በአንድ ጭልፋ ወጥ 11 ሰዓት ላይ ተበልቶ መጠናቀቅ አለበት፡፡ ከዚያ ካለፈ መብራት ስለሌለ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ያውም ምሳ መመገብ የለም፡፡ ፍኖተ ሠላም አቅራቢያ በምትገኘው ማንኩሳ አካባቢ በአንዲት የገጠር መንደር የተወለደ የ25 ዓመት ወጣት ነው፡፡ የነተበ ቲሸርት ለብሷል፡፡ ቁምጣው ጉልበቱን ሳይነካ ታፋው ላይ ቀርቷል፡፡ የቀኑ ፀሀይና የማታው ንፋስ መፈራረቅ ሰውነቱን ከመሬቱ አፈር ጋር አመሣስሎታል፡፡
የቤተሠቡ መሬት ተሸንሽኖ ለታላላቅ ወንድሞች ሲሠጥ ዕድሜው ገና በመሆኑ ከቤተሠቡ ጉያ አልወጣም ነበር፡፡ “መሬት ጠበበ ደካማ ቤተሠቦቼ ላይ ሸክም አልሆንም ጉልበትና ጤና እያለኝ ሊርበኝ አይገባም፤ በዚያ ላይ ዕድሜዬ ለአቅመ አዳም እየደረሠ ነው ብዬ ነበር፤ በ2000 ዓ.ም ወደ ቤኒሻንጉል የሄድኩት›› የሚለው ወጣቱ፤ በያሶ ወረዳ በብርኮ ቀበሌ ኑሮውን ካደረገ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከጉሙዝ ገበሬ የእኩል እያረሠ ሠሊጥ እና በቆሎ እያመረተ በመሸጥ ከራሱ አልፎ ደካማ ቤተሠቦቹን መርዳትም ጀምሮ ነበር፡፡ ወጣቱ እንደሚለው የቋጠረውን ጥሪት ለመሠብሠብ እንኳን ጊዜ ያልሠጠው “የአገራችንን ለቃችሁ ውጡ” ወከባ ባዶ እጁን ፍኖተ ሠላም እንዲመጣ አስገድዶታል፡፡ “በጣም ተስፋ የቆረጥኩት እዛው እያለኹ ነው፡፡ አንድ የክልሉ ፖሊስ ስድስት ሠዓት ላይ አግኝቶኝ ከሁለት ሠዓት በኋላ ስመለስ ባገኝህ በነፍስህ ፍረድ ካለኝ በኋላ ነው›› የሚለው ወጣቱ፤ “ከምሞት ነፍሴን ይዤ ላምልጥ በሚል የምቀይረው ልብስ ሳልይዝ 350 ብር ከፍዬ ወደ ፍኖተ ሠላም መጥቼ መሠሎቼን ተቀላቅያለኹ፡፡ እኔ ጉልበት ኖሮኝ አመለጥኩ፤ እዛው የቀሩት ናቸው የሚያሳዝኑኝ” ይላል፡፡ ተፈናቃዩ ጨርቄን ማቄን ያለ፣ ንብረት እና ቤተሰቡን ለመሠብሠብ የተፍጨረጨረ በድብደባ ለስብራትና ለቁስለት መዳረጉን ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያዊያን እናቶች የመውለጃ ወራቸው ከመግባቱ ቀደም ብሎ እንደየ አቅምና ፍላጐታቸው የገንፎ፣የአጥሚት እህሉ፣ የህፃኑ ልብስና መታቀፊያ ይዘጋጃል፡፡ እናት ምጥ ስትያዝ በቤተሰብ በወዳጅ ዘመድ ትከበባለች፡፡
ሁሉም ጭንቀቷን ይጋራል፡፡ ተፈናቃዮቹ እናቶች ግን ይህ ዕድል ተነፍጓቸው በጠጠራማውና ገመናን በማይሸፍነው ሜዳ ላይ በስቃይ ልጅ እየተገላገሉ ነው፡፡ በዚህ ዐሥር ቀናት ውስጥ እንኳን አራት እናቶች በመጠለያው መውለዳቸው ተነገረኝ፡፡ አንጀት የሚጠግን ምግብ፣ ጐን የሚያሞቅ የረባ ልብስ ለማግኘት አልታደሉም፡፡ እነዚህን አራስ እናቶች ከ3500 ተፈናቃይ መካከል ለመለየት ብቸገርም የዐይን እማኞች ጠቁመውኛል፡፡ ከቤኒሻንጉል ሲባረሩ አራስ የነበሩ ወላጆችም በመጠለያው ይገኛሉ፡፡ ለነፍስ ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ክርስትና ያልተነሱ ሕፃናትን ለይተው ክርስትና ሲያስነሱና ሲያጽናኗቸው እንደነበርም ነግረውኛል፡፡ በ17 ዓመት ወጣት ጀርባ ላይ የታዘለው በዐይን ግምት ሁለት ዓመት የሚኾነው ሕፃን አፍንጫው ተገባብጦ ቆስሏል፡፡ ወንድሜ ነው ያለችኝን ሕፃኑን ያዘለችውን ወጣት ምን ኾኖ አፍንጫው እንደቆሰለ ጠየቅኳት “የምንተኛበት መሬት ደንጊያ ስለሚበዛው ሲንፈራገጥ ልጦት ነው” አለችኝ፡፡ ድንጋዩ እንኳን ለሕፃን ለዐዋቂም እንደሚያስቸግር አስተውያለሁ፡፡ ከዛሬ ስምንትና ዘጠኝ ዓመታት በፊት ከአማራ ክልል ከተለያዩ ቦታዎች የተሻለ ሕይወት ለመኖር እና እየተባባሠ በመጣው የእርሻ መሬት እጦት የተነሳ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማይዞን ያሶ ወረዳ ሀሎ ጥቅሻ፣ ሆኒ፣ ሊጐ፣ ባብርኮ፣ ሻብቲ፣ ድልድል፣ ቲኒጆ መጢና ሌሎችም ቀበሌዎች ኑሯቸውን አደረጉ፡፡
አብዛኛዎቹ በአካባቢው ካሉ የጉሙዝ ተወላጆች ጋር በመስማማትና መሬታቸውን የእኩል በማረስ ጥሪት መቋጠርና የጉሙዝ ተወላጆችንም ሕይወት መቀየራቸውን በአፅንኦት ይናገራሉ፡፡ ጥቂቶች ደግሞ በያሶ ከተማ ንግድ ፈቃድ በማውጣት የንግድ ሥራ ማንቀሣቀስና በሕጋዊ መንገድ ለመንግሥት ግብር እየከፈሉ መኖራቸው ቀጥለው ነበር፡፡ በየዓመቱ በአካባቢው ባለሥልጣናት ውጡ እየተባሉ በስጋት ሲናጡ ይቆዩና ተመልሠው መሥራት እንደሚጀምሩ የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ፤ አብዛኛው ገበሬ ከጉሙዝ ተወላጆች ጋር ተዋዶና ተስማምቶ፣ ጥሪት አፍርቶ ወልዶና ከብዶ ይኖር ነበር፡፡ የዘንድሮው የ “ውጡሉን” ጥያቄ ግን በጥያቄ ብቻ አላበቃም፡፡ እንደ ተፈናቃዮቹ ገለፃ ያለ ማስጠንቀቂያ ንብረትና ቤተሠብ ሳይሠበስቡ እየተደበደቡና እየተንገላቱ አካባቢውን እንደለቀቁ ይናገራሉ፡፡ ከአካባቢው ጉልበት ያለው እየሮጠ፣ አቅመ ደካማው እየተደበደበ፤ እየወደቀና እየተነሳ መውጣት የቻለው ወጥቷል፡፡ የወረዳው አመራሮች መኪኖች እየጫኑ እዲያደርሷቸው ለሹፌሮች ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ፣ ሹፌሮችም አጋጣሚውን በመጠቀም በ300 ብር የሚሔደውን መንገድ ከ350 እስከ 400 ብር እያስከፈሉ፣ የሕዝቡን እንግልት ቢያባብሱትም ዕድለኛ የሚባሉት ነፍሳቸውን ይዘው በፍኖተ ሠላም ከተማ በአንድ የደረቀ መሬት ላይ በብርድና በፀሀይ እየተቆሉ ይገኛሉ፡፡
ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት፤ ከባህርዳርና ከየወረዳቸው ኃላፊዎች መጥተው ስብሰባ እና ፍሬአልባ ውይይት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ፡፡ “በየጐጣችን ያሉ የወረዳው ኃላፊዎች ለችግሩ መፍትሔ እስኪገኝ ወደየቤተሰባችን እንድንገባ ይነግሩናል” ያሉት ተፈናቃዮቹ፤ “እኛ ቤተሰብ አፍርተን እንዴት ደካማ ቤተሰቦቻችን ላይ ሄደን ሸክም እንሆናለን” የሚል ጥያቄ ለኃላፊዎች ሲያነሱ “እኛ ከክልሉ ታዘን እንጂ እንኳን እናንተን አንድ በሽተኛ የሚያስጠጋ እንኳን ቦታ የለንም” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን በመጠለያው ያሉት ተፈናቃዮች ይገልጻሉ፡፡ በድንጋጤና በወከባ ምንም ሳይዙ በመፈናቀላቸው ወደየትውልድ ቀያቸው ቢመለሱ የሚልሱት የሚቀምሱት እንደሌለ በስብሰባው ላይ ለኃላፊዎቹ ሲናገሩ “እንደምንም ተጠጋግታችሁ ተቀመጡ፤ ምንም ልንረዳችሁ አንችልም” ይሉናል፤ በዚህ አይነት ባዶ ሜዳ ላይ ከሚወድቁ እዚሁ ሜዳ ላይ መንግሥት የፈለገውን ያድርገን በሚል ወዴትም የመሄድ ፍላጐት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ “እኛ ከቤኒሻንጉል ስንባረር የክልሉ ተወላጅ ባለመሬቶች ስብሰባ እየተቀመጡ ከወረዳው ባለስልጣናት ጋር ሲሟገቱልን ከርመዋል” የሚለው አንድ ተፈናቃይ፤ “እኛ ምን መብላት እንዳለብንና እንደሌለብን እንድንለይ ያደረጉን እነዚህ ገበሬዎች ናቸው አርሰውና አምርተው ከሚሰጡን ምርት ሚስቶቻችንን ከእንብርክክ የድንጋይ ወፍጮ አውጥተን ዘመናዊ ወፍጮ እስከመትከል እና ባለሀብት እንድንሆን አድርገውናል” ብለው ለያሶ ወረዳ ኃላፊዎች ይነግሩላቸው እንደነበር ተፈናቃዮቹ ይናገራሉ፡፡
የጉምዝ ገበሬዎችን ሰብስበው “እነዚህ ስደተኞች መጀመሪያ ሲገቡ አባባ ይሏችሁ ነበር፣ ከዚያ አቶ እገሌ ማለት ቀጠሉ፣ አሁን ስማችሁን ብቻ ነው የሚጠሩት፣ ነገ ደብድበውና መሬታችሁን ቀምተው፣ ክብራችሁን አዋርደው የቀን ሠራተኛ ያደርጓችኋል፡፡ እነሱ ከመጡ ብዙ ሃብትና ንብረት አፍርተዋል፣ እናንተን እያሰነፉ ራሣቸው ሃብታም እየሆኑ ነው፤ ስለዚህ በአፋጣኝ መውጣት አለባቸው” እያሉ ሊያሳምኗቸው ቢሞክሩም የጉሙዝ ገበሬዎች ከእኛ መነጠሉን አልወደዱትም፤ እየተደበደብን ንብረታችን የትም ተበትኖ ሲቀር እያለቀሱ ሽኝተውናል” ነበር ያለኝ አንዱ ተፈናቃይ፡፡ ተፈናቃዮቹ ወደ ፍኖተ ሠላም ከገቡ ወደ ሦስት ሳምንት እየተጠጋቸው ሲሆን ገና እንደመጡ ያሳረፏቸው ሌላ ቦታ ነበር ፡፡ በዚህም የከተማው ሰውና የሚመለከተው አካል የማያያቸው ቦታ በመሆኑ ከተፈናቃዮቹ ወጣት ወጣቶችና በትምህርታቸው ትንሽ የገፉት ስደተኞችን በማስተባበር መጀመሪያ ካሉበት ቦታ ዋናውን አስፋልት መሃል ለመሃል ይዘው ግር ብለው ወደ አደባባዩ ሲወጡ የከተማው ሕዝብ ግልብጥ ብሎ ወጣ፡፡ ከዚያም የከተማው ኃላፊዎች አሁን ያሉበትን ቦታ እንደሰጧቸውና፣ አሁን ያሉበት ቦታ በፊት ከነበሩበት የሚሻለው ከተማው ውስጥ በመሆኑ የአካባቢው ሰው ለህፃናቱ ውሃም ዳቦም እንዲያቀብላቸው ረድቷቸዋል፡፡ የአካባቢው አርሶ አደር ወደ 15 ኩንታል የሚጠጋ በቆሎ ከማቀጣጠያ እንጨት ጋር ይዞ በመምጣት እየቆላ እንዲመገባቸው ይናገራሉ፡፡ በቄስ መሪነትም ወደ 200 የሚጠጋ እንጀራ ይዘው የደከሙትን እንዲመገቡላቸው ይገልፃሉ፡፡
እንደ ተፈናቃዮቹ ገለፃ በየዕለቱ ለስብሰባ ነው፡፡ መፍትሔ ግን የለም፡፡ ሰው በችጋርና በህመም እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ ቀይ መስቀል አልፎ አልፎ ህክምና ቢሰጥም በቂ አለመሆኑን ነግረውኛል፡፡ አንዲት እናት “በቀን ሁለት ጊዜ ለሚሰጡን ብናኝ እንጀራ 50 ዐይነት ካሜራ እተየደቀነ እንቀረጣለን” ብለው አማረዋል፡፡ እኔ በስፍራው በደረስኩበት ዕለት ከአምስቱ በአንዱ መጠለያ ባለው ሜዳ ላይ ሕዝቡ ጨረቃ መስሎ ተሰብስቦ ነበር፡፡ ነፍሰጡሯ እንደነገረችኝ፤ ከቤኒሻንጉል በመጡት ስደኞች ሰበብ በየቦታው ስደት ሄደው የነበሩ ሁሉ ከእነሱ ጋር ያሰፍሩናል በሚል እየተቀላቀሉ በመሆናቸው፤ አሁን የየወረዳውና የክልል ሃላፊዎች እንለያለን በሚል መታወቂያ እየሰበሰቡ እንደነበር አጫውታኛለች፡፡ መንግሥትን ፍለጋ ተፈናቃዮቹ ከመጡ ሁለት ሳምንት አልፎ ሦስተኛውን ጀምረዋል፡፡ በየጊዜው የየወረዳውና የየ ክልሉ “በአማራ ሰንዲ ወንበርማ በተባለ አካባቢ ቤንሻንጉሎች ሰፍረው በሰላም እየኖሩ ነው፡፡ የእነርሱ ክልል ሃላፊዎች እኛን ጠልተው በግፍ ካባረሩን እነሱ ይውጡና ቦታውን እኛ እንስፈርበት የሚል ጥያቄ ለሃላፊዎቹ አንስተን ነበር” የሚለው አንድ ተፈናቃይ፤ “ይሄ የብሔር ግጭት ስለሚያመጣ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ አይደለም፤ በድጋሚም እንዳታነሱ” በሚል እንዳስጠነቀቋቸው፤ ይገልፃል፡፡ አያይዞም ከዚህ በኋላ የተሻለ መፍትሔ ለማግኘት እስከ 12ኛ ክፍል የተማሩና የተሻለ ብቃት አላቸው ያሏቸውን በመምረጥ ኮሚቴ ማቋቋማቸውን ይናገራል፡፡ በኮሚቴው አማካኝነት ከተፈናቃዩ በነፍስ ወከፍ አምስት ብር ተዋጥቶ ሃያ ሺህ ብር እንደተሰበሰበ የሚናገረው የኮሚቴው አንድ አባል፤ ይህ ሃያ ሺህ ብር በተፈናቃዩ ለተወከሉ ሰዎች ተሰጥቶ መብታቸውን ለማስከበር ለሚደረግ የትኛውም እንቅስቃሴ ሥራ ማስኬጃ ይሆናል ሲል ነበር ያጫወተኝ፡፡
“ ጉዳያችን በየወረዳችን እና በክልሉ መንግሥት እልባት ስላላገኘ፣ የመጀመሪያ ሥራችን ተፈናቃዩን ወክለን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ጽ/ቤት ለመሄድ ዝግጅት ጨርሰናል” ይላል ወጣቱ ተፈናቃይ፡፡ ሃያ ሺህ ብሩም ለዚሁ እንቅስቃሴ የሚውል ነው፡፡ ከመጠለያው ወጥቼ ኳስ ሜዳውን መሃል ለመሀል ሰንጥቄ ወደመጣሁበት ስመለስ አንድ መልከ መልካም ጐልማሣ ከበረዶ የነጣ ጋቢያቸውን ደርበው፣ ከአንድ ወጣት ጋር ሜዳው ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ጥሩ ወዘና ያላቸው በመሆኑ ተፈናቃይ አይመስሉም፡፡ ግምቴም ትክክል ነበር፡፡ ሠላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ስለ ስደተኞቹ አንስቼ መጨዋወት ጀመርን፡፡ “እኔ 58 ዓመት ሙሉ ስኖር የሰው ልጅ እንዲህ ያለ ፈተና ሲቀበል ሳይ የ”በኸሬ” ነው (በአካባቢው አነጋገር የበኸሬ ማለት የመጀመሪያዬ እንደማለት ነው) አሉኝ የአካባቢው ነዋሪ፡፡ “ሰሞኑን አራት ሴቶች እዚህ የምታይው ሜዳ ላይ (መጠለያውን ማለታቸው ነው) ሲወልዱ ስመለከት መፈጠሬን ጠላሁ” በማለት የችግሩን አስከፊነት አስረዱኝ፡፡ ወገን ሲንገላታ ማየት ምን ያህል እንደሚከብድ የተናገሩት የዛው መንደር (የባከል) ነዋሪው ጐልማሳ፤ የተፈናቃዮቹን ችግር ለመስማት “ላህ” የተባለ ወንዝ ሲሄዱ አብረው ሄደው ችግሮቻቸውን እንደሚያዳምጡም አጫውተውኛል፡፡ ምንም እንኳ የእኚህ ሰው ቤት ከመጠለያው ፊት ለፊት ኳስ ሜዳው እንዳለቀ የሚገኝ ቢሆንም ወደ መጠለያው ለመግባት አይደፍሩም፡፡ “ጆሮ ጠቢውና አዋሻኪው ማንና የት እንደሆነ አይታወቅም፤ ከእነሱ ጋር ለመጨዋወት ላህ ወንዝ ነው የምሄደው” በማለት ስጋታቸውን ነግረውኛል፡፡ በዛን ሰዓት ሜዳ ላይ ለምን እንደተቀመጡም ጠይቄያቸው ነበር፡፡ “ይሄ ሁሉ ሰው ሜዳ ላይ እንደጥሬ ፈሶ እንዴት በጊዜ እቤቴ እገባለሁ” የሚሉት እኚሁ የመንደሩ ነዋሪ፤ ሁኔታውን ለመቃኘትና የሰዎችን ሁኔታ ለመታዘብ ሁሌም በዚያ ሰዓት እዛ ቦታ እንደሚቀመጡ ነገሩኝ፡፡ በመጨረሻም “ለመሆኑ አንቺስ ከተፈናቃዮቹ ወገን ነሽ” የሚል ጥያቄ አነሱ፡፡ ለአካባቢው እንግዳ መሆኔን ነግሬያቸው ተሰናበትኳቸው፡፡
Source Addis Admas
Source Addis Admas
No comments:
Post a Comment