Sunday, 14 April 2013

ጋዜጠኛ እና መምህርት ርዕዮት አለሙ በዝግ ታስራ ህክምና ተከልክላ በጡት ካንሰር እየተሰቃየች ነው

በሽብር ተግባር ተፈርዶባት በእስር ላይ የምትገኘው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ በማረሚያ ቤት ከሰዎች ጋር እንዳትገናኝ ለብቻዋ በዝግ ከታሰረች በኋላ፣ በከፍተኛ የጤና መታወክ ውስጥ መሆኗንና ይህም ለሕይወቷ አስጊ መሆኑን የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ በመባል የሚታወቀው ሲፒጄ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም ለፍትሕ ሚኒስትሩ በላከው ደብዳቤ አሳሰበ፡፡
“ይህንን ደብዳቤ የምንጽፈው እ.ኤ.አ. በሰኔ 2011 በሽብር ተግባር ተፈርዶባት በእስር ላይ የምትገኘው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ዝግ በሆነ አንድ ክፍል ውስጥ ከሰው እንዳትገናኝ በማረሚያ ቤቱ ከተደረገ በኋላ፣ የገጠማትን የጤና መታወክ ወደ እርሶ በማድረስ ትኩረት እንዲሰጣት ለማድረግ ነው፤” ይላል ሲፒጄ ለፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ብርሃን ኃይሉ በቀጥታ የላከውና በድረ ገጹ ላይ ያስቀመጠው ደብዳቤ፡፡ 


የጋዜጠኛዋ የቅርብ ሰዎች ለዓለም አቀፍ የሴቶች የሚዲያ ፋውንዴሽን  ርዕዮት ለሁለት ወራት በአንድ ክፍል ውስጥ ለብቻዋ ተዘግቶባት እንድትታሰር መደረጓን መግለጻቸውን ኮሚቴው በደብዳቤው አስረድቶ፣ እሱም በገለልተኛ አካላት ማጣራቱን አስታውቋል፡፡ 

ይህንን መረጃ በመንተራስ ገለልተኛ አካላት ሁኔታውን እንዲያጣሩ ማድረጉን የሚገልጸው ሲፒጄ፣ በዚህም እውነትነቱን እንዳረጋገጠ ለሚኒስትሩ በደብዳቤው አሳውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ርዕዮት የጡት ካንሰር ሕክምና የሚያስፈልጋት መሆኑ በተደረገላት ምርመራ በግልጽ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ማረሚያ ቤት ከገባች ወዲህ የሕክምና ባለሙያ እንዳያያት መደረጉን ማረጋገጡንም በደብዳቤው ገልጿል፡፡

“ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን ለማክበርና ዲሞክራስያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የገባችውን ቃል ጋዜጠኛ ርዕዮት ላለችበት ችግር መፍትሔ በመስጠት እንድታሟላ በጥብቅ እንጠይቅዎታለን፤” በማለት የሲፒጄ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ጆኤል ሲመን ለአቶ ብርሃን ኃይሉ የላኩት ደብዳቤ ያስረዳል፡፡ 

ርዕዮት ቀደም ሲል የተዘጋው የፍትሕ ጋዜጣ ዓምደኛ የነበረችና በውጭ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሪቪው ድረ ገጽ ከአገር ውስጥ ትዘግብ የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህ ድረ ገጽ መንግሥት በሽብር የፈረጃቸው ግለሰብ የሚመሩትና ጋዜጠኛዋም መረጃዎችን ለግለሰቡ በመላክና ለዚህ ተግባሯም ገንዘብ በመቀበል ተጠርጥራ በሽብር ድርጊት በመከሰሷ፣ 14 ዓመት የተፈረደባት ሲሆን፣ በይግባኝ ባደረገችው ክርክር ወደ አምስት ዓመት ዝቅ እንዲልላት መወሰኑ ይታወሳል፡፡ 

No comments:

Post a Comment