Thursday, 1 November 2012

የማሌዥያ ኩባንያ እርሻ በሱርማ ማኅበረሰብ ተጠቃ

 
በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን የፓልም ዘይት ለማምረት 31 ሺሕ ሔክታር መሬት የወሰደው የማሌዥያ ኩባንያ በሱርማ ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ በሚደርስበት ጥቃት ሥራውን በአግባቡ መሥራት እንዳልቻለ ተገለጸ፡፡ ለኩባንያው የተሰጠው የሳር መሬት ሲሆን ከብት አርቢ የሆነው የሱርማ ማኅበረሰብ ቦታውን ለግጦሽ ይጠቀምበታል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከደቡብ ክልል መንግሥት ጋር በመቀናጀት የሱርማን ማኅበረሰብ ከአርብቶ አደርነት ወደ አርሶ አደርነት ወይም ወደከፊል አርሶ አደርነት መቀየር የሚያስችል ዕቅድ አውጥቷል፡፡

ይህንን ዕቅዱን ለማስፈጸም 17 ሺሕ ቤቶችን ገንብቶ ለሱርማ ማኅበረሰብ አካላት ለማከፋፈል የሚያስችለውን ሥራ መጀመሩን የቤንች ማጂ ዞን የኢንቨስትመንት ማስፋፋት የሥራ ሒደት ባለቤት አቶ በላይ አበበ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ አንድ የሱርማ አርብቶ አደር ከ600 በላይ ከብቶች ይኖሩታል፡፡ እነዚህን ከብቶች ይዞ ውኃና ሳር ወዳለበት አካባቢ እንደ ወቅቱ ሁኔታ ይዘዋወራል፡፡

ለማሌዥያው ሊምሲዩጃን ኩባንያ የተሰጠው መሬት የሱርማ ማኅበረሰብ ለግጦሽ የሚጠቀምበት የሳር መሬት ነው፡፡

ሊምሲዩጃን ያካሄዳቸው የእርሻ ሥራዎች በማኅበረሰቡ ተደጋጋሚ ጥቃት እየተሰነዘረባቸው ነው፡፡ ባለፈው ረቡዕ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሰበሰቡት የኢንቨስተሮች ስብሰባ የኩባንያው ተወካይ ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡

ተወካዩ እንዳሉት፣ የሱርማ አርብቶ አደሮች የሚያካሂዱትን ልማት በተደጋጋሚ አጥቅተዋል፡፡ ችግሩም ከበድ ያለ በመሆኑ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መፍትሔ እንደሚፈልጉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ለኩባንያው በሰጡት አስተያየት፣ የሱርማ ማኅበረሰብ ጥቃቱን ያደረሰው ኩባንያው የሚያካሂደው ሥራ እንደሚጠቅመው ግንዛቤ እንዲጨብጥ ባለመደረጉ ነው፡፡ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ቢደረግ ከማንም በበለጠ ፕሮጀክቱን ይደግፋል ሲሉ አቶ ኃይለ ማርያም በአንድ ወቅት በአካባቢው ያጋጠማቸውን በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የማሌዥያው ኩባንያ ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለፓልም ዘይት ልማት የጠየቀው 100 ሺሕ ሔክታር መሬት ነበር፡፡

ኩባንያው በዚህ መሬት ላይ የፓልም ዛፎችን በመትከል የምግብ ዘይት የማምረት ዕቅድ ይዟል፡፡ ነገር ግን መንግሥት የጠየቀውን መሬት በአንድ ጊዜ አላቀረበለትም፡፡ ምክንያቱም እንደ ሥራው አፈጻጸም እየታየ የጠየቀው መሬት ሊሰጠው ይገባል ከሚል አስተሳሰብ መሆኑን አቶ በላይ ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት 31,299 ሔክታር መሬት ተሰጥቶታል፡፡ ይህንን ፕሮጀክት ለማካሄድ 3.72 ቢሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግቧል፡፡

No comments:

Post a Comment