አሜሪካን ሀገር ወደሚኖሩ ወዳጆቼ ቤት ሄጄ ነበር፡፡ ከተጋቡ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ቤታቸው ስገባ የቤቱም ዕቃ የቤቱም ሰዎች ዝምታ ውጧቸዋል፡፡ አባ አጋቶን ቤት የገባሁ ነው የመሰለኝ፡፡ እርሱ ክፉ ላለመናገር ሰባት ዓመት ድንጋይ በአፉ ጎርሶ በአርምሞ ተቀምጧል፡፡ ነገር ዓለሙ አላምር ሲለኝ ‹ምነው ያለ ወትሯችሁ ዝምታ ዋጣችሁ› ብዬ ተነፈስኩ፡፡ እዚህ ቤት የነበረውን ሳቅና ጨዋታ ስለማውቀው፡፡ ‹ሳቅና ጨዋታ ዝና ካማራችሁ› ሲባል አልሰማችሁም፡፡ የመለሰልኝም የለ፡፡ በኋላ ነገሩን ሳጠናው ሁለቱም ተኳርፈዋል ለካ፡፡ ‹‹ለመሆኑ እንዲህ ሳትነጋገሩ ስንት ጊዜ ተቀመጣችሁ› ብዬ ስጠይቅ ስድስት ወር ሆኗቸዋል፡፡ ሁሉም በየሥራው ይውላል፤ ማታ ይመጣል፤ ኪችን ገብቶ ያበስላል፤ በልቶ ቴሌ ቭዥን ያያል፤ ከዚያም ይተኛል፡፡ ቢል ሲመጣ ይህንን እኔ ከፍያለሁ ብሎ አንዱ ወረቀት ጽፎ ይሄዳል፤ ሌላው በተራው ይከፍላል፡፡ ይቺ ናት ትዳር፡፡
ድሮ የሰማሁትን ቀልድ ነበር ትዝ ያሰኙኝ፤ ባልና ሚስቱ ተኳርፋው አይነጋገሩም አሉ፡፡ ቤቱ እንደ መቃብር በጸጥታ ተውጦ ከርሟል፡፡ አንድ ቀን ባል ሌሊት አሥር ሰዓት የሚነሣበት ጉዳይ ገጠመው፡፡ ከተኛ መነሣት የሚከብደው ቢጤ ነበርና የመቀስቀሻውን ሰዓት ሊሞላ ሲስበው ተበላሽቷል፡፡ አዘነም፤ ተናደደም፡፡ ምን ያድርግ፡፡ ባለቤቱ ገና ከሥራ አልገባችም፡፡ ‹የወደዱትን ሲያጡ የጠሉትን ይመርጡ› ነውና፡፡ በቁራጭ ወረቀት ላይ ‹አሥር ሰዓት ላይ ቀስቅሽኝ› ብሎ ጽፎ በራስጌው ባለው ኮመዲኖ ላይ አስቀመጠና ተኛ፡፡ ሚስቱ ስትመጣ አየችውና ስቃ ተኛች፡፡ ልክ ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ነቃችና በዚያው በቁራጭ ወረቀት ላይ ‹አሥር ሰዓት ሆኗልና ተነሣ› ብላ ጽፋለት ተኛች፡፡ እርሱ ዕንቅልፉን ለጥጦ ለጥጦ ሲነሣ ነግቷል፡፡ ተናደደ፤ ግን እንዳይናገራት ለካስ ተኳርፈዋል፡፡ እዚያው ወረቀት ላይ ‹በጣም ታሳዥኛለሽ› ብሎ ጻፈላት፡፡
እነዚህ ወዳጆቼ ይህን ነበር ያስታወሱኝ፡፡ አሁን እንዲህ ያለው ኑሮ ምን ዓይነት ኑሮ ይባላል? ብዬ ስም ፍለጋ ብዙ ጊዜ አሰብኩ፡፡ ይህን እያሰብኩ እያለ አንድ ዕቃ ለመግዛት ‹ካስኮ› ወደሚባለው አሜሪካ ውስጥ ካሉት ታላላቅ መደብሮች ወደ አንዱ ከእነዚሁ ወዳጆቼ ጋር ተጓዝን፡፡ እዚያ መኪናችን ለማቆም አራት የፓርኪንግ ፎቆችን መውጣትና እንደ አዲስ አበባ ስታዲዮም የተለጠጠውን ሰፊ የማቆሚያ ሜዳ ማካለል ነበረብን፡፡ ለዓይን እስኪያታክት ድረስ መኪኖቻ ተኮልኩለውበታል፡፡ በዓይነት ባይነታቸው፡፡ ረዥም፣ አጭር፣ ሽንጣም፣ ቁመታም፤ ያበጠ፣ የከሳ፣ ግልጽ፣ ድፍን፣ ነጭ፣ ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ፣ ሰማያዊ፣ ወይን ጠጅ፣ ምኑ ቅጡ፤ ተደርድረዋል፡፡ ጎን ለጎን፣ ፊትና ኋላ፤ በኋላ መመልከቻቸው ሊነካኩ እስኪደርሱ ድረስ ተደርድረዋል፡፡ የሚገርመው ግን አንዱ ከሌላው ጋር አያወሩም፣ አይጫወቱም፣ ኧረ እንዲያውም አይተዋወቁም፤ አንድ ያደረጋቸው በአንድ የፓርኪንግ ሜዳ መቆማቸው፣ ጎን ለጎን መሆናቸው፣ በአንድ ጣራ ሥር ውሎ ማደራቸው ብቻ ነው፡፡ የዚያኛውን ጠባይ፣ ሥሪት፣ ዓላማና፣ የኑሮ ጓዳ ይህኛው አያውቅም፤ እንዴው በአንድ ፓርኪንግ ቦታ ብቻ አብሮ ቆሞ ማደር፡፡ እነርሱምኮ ‹ቢል› አለባቸው፡፡ የፓርኪንግ ቢል፡፡
ያኔ ስም አገኘሁለትና እነዚህን ወዳጆቼን ‹የእናንተ ኑሮኮ ፓርኪንግ ነው› አልኳቸው፡፡ ሁለቱም ወደ እኔ ዞሩ፡፡ ‹እስኪ እነዚህን መኪኖች እዩዋቸው፤ አይፋቀሩ፣ አይጣሉ፣ አያወሩ፣ አይጫወቱ፣ አይወያዩ፣ አብረው አይሠሩ፣ አብረው መከራ አይካፈሉ፣ አብረው አይደሰቱ፤ ግን በአንድ የፓርኪንግ ቦታ ቆመዋል፡፡ ሁሉም በየራሱ መጥቶ ቆመ፡፡ ሁሉም በየራሱ ተነሥቶ ይሄዳል፡፡ የእናንተስ ከዚህ በምን ተለየ፡፡ ሁለታችሁም በየራሳችሁ ትውላላችሁ፤ ማታ ስትመጡ ቤታችሁ ውስጥ ፓርክ ታደርጋላችሁ፤ በቃ› ከልባቸው ነበር የሳቁት፡፡ ፍርስ እስኪሉ፡፡ ለሰው አንድ ቦታ መሥራት፣ አንድ ቦታ መኖር፣ አንድ አልጋ መተኛት፣ በአንድ ቢሮ መዋል፣ አንድ ሕንፃ ላይ መኖር ብቻውን ከሰው ጋር መኖር አያሰኘውም፡፡ ይኼንንማ መኪኖችም ይኖሩታልኮ፡፡ ያውም ሰላማዊ በሆነና ማንም ማንንም ሳይነካ፣ ማንም በማንም ቦታ ላይ ሳይደርስ፤ ግን ይህ ፓርኪንግ እንጂ ኑሮ አይደለም፡፡ ኑሮ ያፋቅራልም ያጣላልም፤ ያገናኛልም፣ ያወያያልም፤ ኑሮ መስተጋብር አለው፡፡ አንደኛው በሌላው ውስጥ ቦታ ሊኖረው ይገባልኮ፡፡
ወዳጅነትኮ አብሮ ከመዋልና ከመኖር፣ ከመሥራትም በላይ ነው፡፡ አንቺ ባልሽ ሳይደውል ሲቀር ሲጠፋ፣ ያስለመደሽ ነገር ሲቀር፣ አንዳንድ ነገሩ ሲለወጥ ቅር የማይልሽና ምንም የማይሰማሽ ካልሆነ ድሮም ትዳር ሳይሆን ፓርኪንግ ነበር የመሠረታችሁት፡፡ እስኪ ያንን መኪና ተመልከቱት ተነሥቶ ሄደ፤ ከጎኑ ያለው መኪና ምን ተሰማው? ምንም፡፡ ሌላው ደግሞ መጣ፤ አያችሁ ፓርኪንግ ሲሆን እንደዚህ ነው፡፡ ወዳጅህ ቢኖር ባይኖር፤ ሰላም ቢልህ ባይልህ፣ ቢመጣ ባይመጣ፣ ካንተ ቢለይ፣ ባይለይ ምንም ካልመሰለህ ይህ ፓርኪንግ እንጂ ወዳጅነት አይደለም፡፡
ለአንዳንድ ሰዎች ወዳጅነት ማለት በፈለጉበት ጊዜ መጥተው ሊያቆሙበት የሚችሉ ፓርኪንግ ይመስላቸዋል፡፡ አይደለም፡፡ ወዳጅነት ጎን ለጎን አይሆንም፡፡ ወዳጅነት አንዱ በሌላው ውስጥ ቦታ ሲኖረው ነው፡፡ ለዚህ ነው ያ ወዳጅህ ሲቀር ክፍተት የሚሰማህ፡፡ ‹ሰው ቢሄድ ሰው ይመጣል› እያሉ የሚዘፍኑ አሉ፡፡ እነዚህ ፓርኪንግ እንጂ ወዳጅነት የማያውቁ ናቸው፡፡ በወዳጅነት ውስጥ ‹ሰው ቢሄድ ሰው ይመጣል› የሚባል መፈክር ተይዞ ሲቀበሉና ሲሸኙ መኖር አይቻልም፡፡ ዘላቂ ወዳጅ የሌለው ፓርኪንግ ብቻ ነው፡፡ እርሱም እንኳን አንዳንዴ ለአንድ ሰው ተመድቦ ይሰጣል፡፡
አሁን አሁንማ በኛም ሀገር የፓርኪንግ ኑሮ እየተለመደ ነው፡፡ ጎረቤቱን የማያውቅ መንደርተኛ፣ ግድግዳ የሚጋራውን የማያውቅ ባለ ኮንዶሚኒየም፣ አብሮ ነዋሪውን የማያውቅ ደባል እየመጣ ነው፡፡ በአንድ ሕንፃ ላይ እየሠሩ ፈጽሞ የማይተዋወቁ ሰዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ እንዲያውም አንድ ወዳጄ ለአንድ የሥራ ጉዳይ አንድ ባለሞያ ይፈልግ ነበርና አንድ ወዳጁ ስልክ ይሰጠዋል፡፡ ጎበዝ ባለሞያ ነው በዚያውም ተዋወቀው ይለዋል፡፡ ስልኩን ተቀብሎ ይደውልለትና ስለ ሥራው ይነጋገራሉ፡፡ ይግባባሉ፡፡ እጅግ የተሻለው ነገር በአካል መነጋገሩ ነበርና ‹ቢሮህ የት ነው› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ አድራሻውን ሲነግረው እዚያ እርሱ ያለበት ሕንፃ ላይ ነው፡፡ የቢሮ ቁጥሩን ይጠይቀዋል፡፡ እጅግ የሚገርመው ነገር የዚያ ባለሞያ ቢሮ ከእርሱ ቢሮ ጎን ነበረ፡፡ ሦስት ዓመት ሠርተዋል አይተዋወቁም፡፡ አያችሁ ፓርኪንግ እንዲህ ያደርጋል፡፡
ቤት ሲገቡ እርሱ ቴሌቭዥን ይከፍታል፣ እርሷም ኪችን ትገባለች፣ እርሱ ይተኛል፣ እርሷ ስልክ ላይ ናት፤ ልጆች ጌም ያጫወታሉ ወይም የሕፃናት ፊልም ያያሉ፤ እንግዳም ፎቴው ላይ ተቀምጦ ይተክዛል ወይም ያንጎላቻል፡፡ እንዲህ እየሆነኮ ነው ኑሮ፡፡ ኑሮ ፓርኪንግ ሲሆን፡፡ በዚህ ዘመን ትልቁ ቅጣት ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? የፓርኪንግ ኑሮ በሚኖሩ ሰዎች ቤት እንግዳ ሆኖ መሄድ፡፡
ቀደምቶቻችንማ አካባቢን የሚያስተሳሥሩ አያሌ ገመዶች ፈትለው ነበር፡፡ ዕድሩ፣ ዕቁቡ፣ ሰንበቴው፣ ማኅበሩ፣ ቡና መጠራራቱ፣ ግብዣ መገባባዙ ሠፈርተኛውን ያቀራርበው ነበር፡፡ ማቀራረብ ብቻ ሳይሆን ለመረዳዳትም አስችሎት ነበር፡፡ ከዚያም ባለፈ የአካባቢው ጸጥታ እንዲጠበቅ ያደርገው ነበር፡፡ የሠፈሩ ሰው፣ የሠፈሩ ልጆች ስለሚታወቁ የማይሆን ሰው መጥቶ የማይሆን ሥራ ለመሥራት አይመቸውም ነበር፡፡ የተጣላ ሰው ቢኖር እንኳን ከእነዚያ ማኅበራዊ ሁነቶች በአንዱ ሲቀር ‹ምን ሆኖ ነው›Lይባላል፡፡ ይታወቃል፡፡ አስታራቂም ይላካል፡፡
አሁንኮ መዋደዳችንም መጣላታችንም ሊታወቅ አልቻለም፡፡ በሠፈራችን ውስጥ እጅግ የረቀቀ ወንጀል ቢሠራ እንኳን ሁሉም ግቢውን ብቻ ስለሚያውቅ የሚከላከለው አይገኝም፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ታላላቅ የመኖርያ ግቢዎች መኪኖቻቸው የሚተዋወቁትን ያህል እንኳን የማይተዋወቁ ጎረቤታሞች አሉ፡፡ መኪኖቻቸው እንኳን አንዳንድ ቀን መንገድ ዘጋህ ብለው በጡሩንባ ይነጋገራሉ፡፡ ባለቤቶቻቸው ግን እንደተዘጋጉ ናቸው፡፡
‹ሠፈራችን› እንለው የነበረውኮ ስለተወለድንበትና ስላደግንበት ብቻ አልነበረም፡፡ እዚያ አካባቢ ብዙ ትዝታዎች አሉን፡፡ የወንዙ፣ የጭቃው፣ የኳስ ጨዋታው፣ የተደባደብነው፣ የጠፋነው፣ የተመረቅነው፣ የተረገምነው፣ አብረን ትምህርት ቤት የሄድነው፣ የመለያ ምት እንደሚጠብቅ ቡድን በመሥመር ተቃቅፈን የተጓዝነው እነዚህ ሁሉ ናቸው ሠፈር› ማለት፡፡ አሁን የሠፈር ልጆች የሌላቸው ልጆች እያሳደግን ነው፡፡ አብረው ሆያ ሆዬ የማይሉ፣ ኳስ የማይጫወቱ፣ ሰኞ ማክሰኞ የማይጫወቱ፣ ሾላ እርግፍ እርግፍ የማይሉ፣ ጢብ ጢብ የሌላቸው፣ አኩኩሉን በተረት ብቻ የሚያውቁ ልጆች እየመጡ ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ የፓርኪንግ ውጤት ነው፡፡
እና ወዳጆቼ፣ ኩርፊያና ግጭት ይኖር ይሆናል፡፡ እንኳን ሰውና ሰው ጉልቻና ጉልቻ እንኳን ይጋጫል ይባላል፡፡ ግን ልክና መጠን ያስፈልገዋል፡፡ እንዲህ አንድ ቤት እየኖራችሁ ለረዥም ጊዜ ከተዘጋጋችሁማ እናንተ ፓርኪንግ ሜዳ ላይ የቆማችሁ መኪኖች እንጂ ምኑን ወዳጆችና ባለትዳሮች ሆናችሁት፡፡ እንደሳቁ ዕቃችንን ገዝተን እንደሳቁ ቤታቸው ገባን፡፡ ይኼው ዛሬም እየሳቁ ይደውሉልኛል፡፡
Daniel Kibert
No comments:
Post a Comment