Wednesday, 14 November 2012

ፍርደኛው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲወረስ ጥያቄ በቀረበበት ንብረቱ ጉዳይ አልከራከርም አለ

አቶ አንዱዓለም አራጌም ፍርድ ቤት ቀርበዋል
በታምሩ ጽጌ

በዚህም ምክንያት ወደ ፍርድ ቤት ከዛሬ በኋላ እንዳልቀርብ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ይሰጥልኝ፤” በማለት አመልክቷል፡፡
 
በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሶ በ18 ዓመታት ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ውሳኔ ያሳረፈበት ፍርደኛው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ዓቃቤ ሕግ እንዲወረስ ስለጠየቀበት የንብረት ጉዳይ ቤተሰቡም ሆነ እሱ መከራከር እንደማይፈልጉ ለፍርድ ቤቱ አስታወቀ፡፡ በነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም. የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሽብርተኝነት አዋጁ በተቀመጠው አንቀጽ መሠረት፣ “በሽብር ወንጀል የተቀጣ ግለሰብ ንብረት መወረስ እንዳለበት ያዛል” በሚል ለፍርድ ቤት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ ንብረታቸው እንዲወረስ ከተጠየቀባቸው ፍርደኞች መካከል በዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ የተወሰነበት አንዱዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ትናንትና ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው የነበሩት የአንድነት ፓርቲ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌና ባለቤታቸው ዶክተር ሰላም አስቻለው፣ እንዲወረስባቸው የተጠየቀውን አንድ የቤት መኪና በሚመለከት ተቃውሞ እንዳላቸው ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

ሌላው ዓቃቤ ሕግ ንብረቱ እንዲወረስ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ያቀረበበት፣ በሌለበት ጥፋተኛ ተብሎ በ15 ዓመታት ፅኑ እሥራት እንዲቀጣ የተወሰነበትና ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው አበበ በለው ሲሆን፣ ባለድርሻ ይሆናሉ ያላቸውን የባለቤቱ አድራሻ ማግኘት አለመቻሉን ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት አመልክቷል፡፡

በመቀጠል ጋዜጠኛ እስክንድር ከተቀመጠበት የተከሳሾች መቀመጫ ሳጥን ውስጥ ቆሞ የሚያቀርበው ሐሳብ እንዳለው በመግለጽ፣ “እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በንብረት ውርስ ምክንያት መከራከር አንፈልግም፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ፍርድ ቤት ከዛሬ በኋላ እንዳልቀርብ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ይሰጥልኝ፤” በማለት አመልክቷል፡፡


የአቶ አንዱዓለም አራጌ ባለቤት ዶክተር ሰላም ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የተቃውሞ ደብዳቤ እንዲወረስባቸው የተጠየቀው የቤት መኪና፣ በዕድሜ ልክ የተቀጡት ባለቤታቸው ስንቅ ማመላለሻና ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ማድረሻና መመለሻ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁሉንም ወገኖች ሐሳብ ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ለአቶ አበበ በለው ባለቤትና ለጋዜጠኛ እስክንድር ባለቤት መጥርያ እንዲደርሳቸውና መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ በማዘዝ፣ የሚቀርበውን መቃወሚያ ለማየትና ውሳኔ ለማስተላለፍ ለኅዳር 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ጋዜጠኛ እስክንድርና አቶ አንዱዓለም በሽብርተኝነት ወንጀል የተጣለባቸውን የቅጣት ውሳኔ በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረቡት የይግባኝ ማመልከቻ ላይ ክርክር እንዲያደርጉ ለኅዳር 13 ቀን 2005 ዓ.ም. መቀጠሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment