Wednesday, 28 November 2012

የብር ምንዛሪ አቅም እየወረደ ነው

በሁለት ዓመት ከ10 በመቶ በላይ ቀንሷል
በዳዊት ታዬ
 
የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ በ17 በመቶ ጨምሮ በ16.35 ብር እንዲመነዘር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መወሰኑ ይፋ ከተደረገበት መስከረም 2003 ዓ.ም. ወዲህ ባሉት ሁለት ዓመታት፣ የብር ምንዛሪ አቅም እየቀነሰ ከ10 በመቶ በላይ መውረዱ ተመለከተ፡፡በኅዳር 2004 ዓ.ም. የየዕለቱ የውጭ ምንዛሪ ዋጋን በሚያመለክተው መረጃ መሠረት የአንድ ዶላር አማካይ የምንዛሪ ዋጋ 17.211 ብር የነበረ ሲሆን፣ በኅዳር 2005 ዓ.ም. ያለው መረጃ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ ወደ 18.181 ብር ማደጉን ያሳያል፡፡

ከኅዳር 2003 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 2004 ዓ.ም. የነበረው የምንዛሪ ዋጋ ከ5.3 በመቶ በላይ ሲጨምር፣ በ2005 በጀት ዓመት የኅዳር ወር የምንዛሪ ዋጋ በአማካይ ወደ 18.181 ብር ማደጉን ተከትሎ ከሌሎች መገበያያ ገንዘቦች አኳያ (በዋናነት ከዶላር) የብር የመግዛት አቅምን በአንድ ዓመት ከ5.56 በመቶ በላይ እንዲወርድ አድርጎታል፡፡ በአጠቃላይ ከኅዳር 2003 ዓ.ም. ወዲህ የብር የመግዛት አቅም በ30 ከመቶ እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየው የምንዛሪ ለውጥ ግን በመስከረም 2003 ዓ.ም. በብሔራዊ ባንክ በአንዴ ከተደረገው ጭማሪ በተቃራኒው ቀስ በቀስ በየዕለቱ ይካሄድ በነበረው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ ተመርኩዞ እየጨመረ የመጣ ነው፡፡ ቀስ በቀስ የታየው ለውጥ በፍጥነት እያደገ የመጣው ደግሞ ካለፈው መጋቢት 2004 ዓ.ም. ወዲህ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየው የምንዛሪ ለውጥ ብሔራዊ ባንክ የብር ምንዛሪ ለውጥ በአንዴ ከማድረግ ይልቅ፣ ቀስ በቀስ እየጨመረ እንዲሄድ ማድረግ መምረጡን ያሳያል የሚሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ10 በመቶ በላይ የደረሰው ጭማሪ ከፍተኛ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

የብር ምንዛሪ ለውጡን በአንድ ጊዜ ከመለወጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደታየው ቀስ በቀስ እንዲለወጥ ማድረጉ በአንድ በኩል የተወሰነ ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ የዋጋ ግሽበት እንዳይወርድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ፡፡



በ2003 ዓ.ም. በአንድ ጊዜ የ17 በመቶ የምንዛሪ ለውጥ መደረጉን ተከትሎ የዋጋ ግሽበት ተከስቷል፡፡ ባለሙያዎቹ ምንም እንኳ ለዋጋ ግሽበት መከሰት ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውሰው፣ ለውጡ ቀስ በቀስ መካሄዱ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የተጋነነ ዋጋ እንዳይኖር ረድቷል ይላሉ፡፡ ሆኖም ቀስ በቀስ የተደረገው ለውጥ አገሪቱ ከፍተኛ የብር ምንዛሪ ለውጥ ያደረገች መሆኑን ጠቋሚ በመሆኑ፣ ለመሠረታዊ ዕቃዎች ዋጋ መጨመር ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ እንደሚገልጹት፣ የዋጋ ግሽበት በሚፈለገው ደረጃ ሊቀንስ ካልተቻለባቸው ምክንያቶች አንደኛው የብር አቅም መዳከምና የውጭ ምንዛሪ ጉልበት በየጊዜው እያደገ መምጣቱ ነው፡፡

ይህም ማለት በኅዳር 2003 ዓ.ም. በአምስት ሺሕ ዶላር ተገዝቶ ከውጭ ይመጣ የነበረ ምርት በወቅቱ ምንዛሪ ዋጋ 82,752 ብር ይፈልግ ነበር፡፡ ይኼው ተመሳሳይ ምርት ከሚመጣበት አገር ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አልተደረገበትም ተብሎ ቢታሰብ፣ በኅዳር ወር 2004 ዓ.ም. ለተመሳሳይ የዶላር መጠን 86,055 ብር ይጠይቃል፡፡ አሁንም ይኼው ምርት ዋጋው ሳይለወጥ በቀድሞው ዋጋ እየተገዛ ነው ቢባል፣ ለአምስት ሺሕ ዶላር በዚህ ወር የሚፈለገው ከ90,905 ብር ነው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌላ የኢኮኖሚ ባለሙያ እንደሚሉት ደግሞ፣ ብሔራዊ ባንክ በአንድ ጊዜ የምንዛሪ ለውጥ ከማድረግ ይልቅ በሳምንት ወይም በወር አዝጋሚ የምንዛሪ ለውጥ ማድረግን መርጧል ይላሉ፡፡ በዚህም አሠራሩ እንደ ቀድሞው በአንድ ጊዜ 15 በመቶ ወይም 20 በመቶ የሚደርስ የምንዛሪ ለውጥ ከሚያደርግ፣ ቀስ በቀስ የምንዛሪ ለውጥ እያስኬደ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ በየጊዜው የሚደረገው ጭማሪ የኢትዮጵያ ብር ከሌሎች የውጭ ገንዘቦች ጋር ያለውን የመግዛት አቅም ይበልጥ እያወረደው ስለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

1 comment:

  1. Excellent .. Amazing .. I’ll bookmark your site and take the feeds also…I’m happy to find so many useful info here in the post, we need work out more techniques in this regard, thanks for sharing.

    By : daycare jakarta

    ReplyDelete