Friday, 2 November 2012

በህልሜ!

ከመሃመድ ሀሰን

40-60 ቤት ለመመዝገብ ሳር-ቤት አካባቢ ቀበሌ 03 ተሰልፍያለሁ፡፡ ትከሻዬን ሲከብደኝ ከኃላዬ የተሰለፈውን ሰው ለማየት ዞርኩኝ፡፡ አቶ ኃይለማርያም ናቸው፡፡ ክው አልኩኝ!

‹‹ምነው በሰላም ነው?›› አልኳቸው የተረጋጋሁ ለመምሰል እየሞከርኩ፡፡

‹‹በሰላም ነው...ያው ለ40-60 የቀበሌ መታወቂያ ለማሳደስና ቤት አልባ መሆኔን ማረጋገጫ ለማውጣት ነው፡፡›› ‹‹አንተስ?›› አሉኝ፡፡

‹‹እኔም እንደዚያው ነው››

‹‹ወረፋ ታስቀድመኛለህ!? በጠዋት ቤተመንግስት የቀጠርኳቸው አምባሳደሮች ስላሉብኝ ነው...! ››

‹‹ይቅርታ እኔ ራሴ ክላስ ትቼ ነው የመጣሁት እቸኩላለሁ›› አልኳቸው፡፡

‹‹ምን ይሻላል ባካችሁ!›› ብለው ተከዙ፡፡ ሲተክዙ ወደሰማይ አንጋጠው በመሆኑ ርዕይ የሚያዩ ይመስላሉ፡፡

‹‹የት ነው የምትሰራው?››

‹‹መቀሌ አስተማሪ ነኝ፡፡››

‹‹እርስዎስ?››

‹‹እኔም አርባምንጭ አስተማሪ ነበርኩ፡፡ አሁን እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ክፍት የስራ ቦታ ወጥቶ እዛ ገብቻለሁ፡፡ በቲቪ አይተኸኝ አታውቅም?

‹‹ኸረ እኔ ቲቪ አላይም...››

‹‹እውነትህን ነው?››

‹‹ምን አስዋሸኝ፡፡ ረዥም ጊዜ ነው ቲቪ ካየሁ....እና ....አዲሱ ስራ አሪፍ ነው? ወደዱት?››

‹‹ምንም አይልም፣ ትንሽ ስራ ይበዛዋል፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲ ነጻነት የለውም፡፡ በጌታ ፍቃድ እወጠዋለሁ ብያለሁ››

‹‹መበርታት ነው እንግዲህ›› አልኳቸው፡፡

‹‹እኔ ምልህ ቤቱ በስንት ዓመት የሚደርሰን ይመስልሀል?››

‹‹ቶሎ የሚደርስ እንኳ አይመስለኝም፡፡ ግን ከዚህ በፊት ኮንዶሚንየም ሳልመዘገብ ስላመለጠኝ በድጋሚ እንዳልጸጸት ብዬ ነው የምምዘገበው››

‹‹እሱስ እውነትህን ነው፡፡ እኔ ምልህ! አራት ኪሎ አካባቢ ኮንዶሚንየም ኪራይ ይገኛል እንዴ ? ከስራዬ ጋር እዚያ አካባቢ ባገኝ ይቀርበኝ ነበር››

‹‹አራት ኪሎ ቱሪስት ጀርባ ኮንዶሚንየሞች አሉ መሰለኝ፡፡››

‹‹ስንት ይሆናል?››

‹‹ባለ ሁለት መኝታ እስከ 4ሺህ 500 አይሆንም ብለው ነው?››

‹‹በእየሱስ ስም!›› ደሞዜ ራሱ 6ሺ አይሞላም እኮ፡፡ ምን በልቼ ልኖር ነው?››

እንደምንም ማብቃቃት ነው እንግዲህ፡፡ ወይም ለምን ቀበና አካባቢ አይከራዩም፤ ዋጋ ረከስ ይላል፡፡ ለአራት ኪሎም ቅርብ ነው፡፡

‹‹እውነትህን ነው...ቀበና ጥሩ ሳይሆን አይቀርም፣ ባለ አራት መኝታ እዚያ አካባቢ ስንት አገኛለሁ?››
ከት ብዬ ሳቅሁ፡፡ ‹‹ባለ አራት መኝታ የሚባል ኮንዶሚንየም የለም፡፡ እየቀለዱ ነው አይደል?››

ኖኖ! እንዴት በዚህ ዘመን እቀልዳለሁ፡፡ ለምንድነው የሌለው?

‹‹አልተሰራማ!›› አልኳቸው፡፡

‹‹ለምን አልተሰራም?››

‹‹እኔ ምን አውቄ! አራት ኪሎ ነው የምሰራው አላሉም እንዴ! እርሶ ይንገሩኝ እንጂ፡፡››

‹‹አንተ ደሞ! ገና ስራ መጀመሬ ነው አልኩህ እኮ! ሶስት ሳምንትም አልሞላኝ፡፡››

‹‹ሁለት መኝታ ታዲያ ጥሩ እኮ ነው፣ አይበቃዎትም?፡፡››

ሶስት ሴት ልጆች አሉኝ፣ በሁለት መኝታ እንዴት ተኩኖ ይኖራል?

‹‹ያው ማብቃቃት ነው!››አልኳቸው፡፡

‹‹እኔ ምልህ!?ይሄ ሁሉ ግን ቤት የሌለው ነው?›› ነው እያጋነኑ ነው? እንዲህ ከሆነማ ቤት የሌለውን ከሚመዘገቡ ቤት ያላቸውን ቢመዘግቡ ለአሰራር ይመች ነበር፤ አይመስልህም?፡፡››

‹‹ትክክል ብለዋል!››

‹‹በዚህ ወረፋ ከሰዓትም የሚደርሰኝ አይመስለኝም!›› 4ኪሎ ደርሼ ብመለስ ይሻላል፡፡

‹‹ይቅርብዎ!ታክሲ አያገኙም፡፡ እዚሁ ተሰልፈው ቢጠብቁ ነው የሚሻልዎት››

‹‹አይ...የሚያደርሰኝ መኪና አለ›› ነጫጭ 3 ኮብራዎችን ከርቀት አሳዩኝ፡፡ ሌሎች ሶስት ጥቁር መነጽር ያደረጉ ወጠምሻዎች መኪናዎቹ ዙርያ ፈንጠርጠር ብለው ቆመዋል፡፡ ወደኔ እያዩ ገለማመጡኝ፡፡

‹‹ምንድናቸው እነዚያ››

‹‹ጠባቂዎቼ ናቸው››

‹‹ከምንድነው የሚጠብቅዎት?››

ፈገግ አሉ! ለመጀመርያ ጊዜ ፍንጭት መሆናቸውን አየሁ፡፡

No comments:

Post a Comment