Tuesday 19 May 2015

ጉዳዩ፡ፕሮግራም ስለማቋረጥ





ርጅታችን ከጣቢያችሁ የአንድ ሰዓት የስርጭት ጊዜ በመውሰድ በ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ላለፉት ሁለት ዓመታት “ጆሲ ኢን ዘ ሃውስ ሾው ” የተሰኘ ፕሮግራም እያቀረበ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ፕሮግራሞቻችን ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው፤ ትውልድን የሚያንጹና የሚያስተምሩ በመሆናቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ለማግኘት የቻሉ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ቀደም ባለው ጊዜ በተፈቀደልን የአየር ሰዓት የሠራናቸውን ፕሮግራሞች ለማቅረብ የነበሩት ሁኔታዎች የተመቻቹ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን አየር ላይ እንዲውሉ ከላክናቸው ፕሮግራሞች አንዳንዶቹ በተፈቀደልን የአየር ሰዓትና ጊዜ እንዳይተላለፉ ተደርገዋል፡፡

ጆሲ መልቲሚዲያ የሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች የአየር ሰዓት ለመሸፈን ብቻ ተብለው የሚዘጋጁ ሳይሆን እያዝናኑ የሚያስተምሩ ኢትዮጽያዊ አንድነትን የሚያጠነክሩ ፤የትላንትን ታሪክ የሚያውሱና ትውልድ የሚቀርጹ፤ መረዳዳትንና መተጋገዝን የሚሰብኩ ናቸው ፡፡ 

በአብዘኛው የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ አገዛዝ መዳፍ ውስጥ በነበሩት ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የጣልያንን ወራሪ ጦር ያሸነፈችበት የአድዋ ድል 119ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በድሉ እንደሚኮራ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በያገባኛል ስሜት ደክመን የሠራነው የአድዋ ድል መታሰቢያ ፕሮግራም በተፈቀደልን ቀንና የአየር ሰዓት እሁድ የካቲት 29 ቀን 2007 ዓ.ም ከሁለት ሰዓት እስከ ሶስት ሰአት እንዳይተላለፍ ተደረጎብናል ፡፡ይህ ያልተለመደ ነገር ሲከሰት ብናዝንም ቀደም ሲል የነበረንን መልካም የሥራ ግኑኙነት ከግምት ውስጥ በማስገባትና ወደፊትም እንደማይደገም በማመን ነገሩን በትዕግስት አልፈን አብረን ለመስራት ሞክረን ነበር፡፡

ይህ መፈጠሩ እያሳዘነን እያለ ሌላ ነገር ተከሰተ፡፡ ድርጅታችን በጣቢያቸሁ ፕሮግራም ማስተላለፍ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ በሀይማኖታዊና በዘመን መለወጫ በዓላት ላይ በተለያየ ጊዜና ሙያ ሀገራቸውን ያገለገሉ ግን ደግሞ የተዘነጉ የሀገር ባለውለታዎችን መጠየቅና የተቻለውን ያህል ድጋፍ ማድረግ የተለመደ ነበር፡፡በእዚህም መሰረት የ2007 ዓ.ም የትንሣኤን በዓልን ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀነው ፕሮግራም በቂና አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት እንዳይተላለፍ ተደርጎብናል፡፡

ፕሮግራማችን በተደጋጋሚ በተለመደው የአየር ሰዓት እንዳይተላለፍ መደረጉ እያሳዘነን እያለ ፤በየመን ፤በደቡብ አፍሪካ በተለይም በሊቢያ አይ.ኤስ የተባለው ፅንፈኛ ቡድን በንጹሃን ዜጎቻችን ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ እንደ ኢትዮጵያዊ አዝነን ፤ቤተሰቦቻቸውን እና ዘመዶቻቸውን በሞት ከተነጠቁ ሀዘንተኞች ጎን ሆነን ሀዘናችን ገልጸንና የሀዘናቸው ተካፋይ ሆነን ድጋፍም አድርገን በተጨማሪም በኢትዮጵያዊ አንድነት ፤በሀይማኖት እኩልነት ፤ተፈቃቅሮ ፤ተቻችሎና ተከባብሮ በመኖር፤ እርስ በእርስ በመረዳዳት እንዲሁም ዜጎቻችንን ለእንግልትና ለሕልፈተ ሕይወት እየዳረገ ባለው ሕገ ወጥ ስደትና ሕገ ወጥ ደላሎች ዙሪያ ደክመን የሰራነው አስተማሪ ፕሮግራም ከጣቢያው በወሰድነው የአየር ሰዓት ላይ በተደጋጋሚ እንዳይተላለፍ መደረጉ ወደፊት አብሮ የመስራታችንን ነገር በጥርጣሬ እንድንመለከተው አድርጎናል ፡፡ 

ፕሮግራማችን በጣቢያችሁ ላይ መቅረብ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለነበረን መልካም ግንኙነት ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ከላይ ከጠቀስናቸው ችግሮች በተጨማሪ ሌሎችም ምክንያቶች ቢኖሩም የስራ ግኑኝነታችን እንዲቀጥል ስምምነት ለማድረግ ብንሞክርም አልተሳካም ፡፡ በእናንተ በኩል እየተከናወነ ያለው ያልተለመደ ተግባር የስራ ግኑኝነታችን እንዲቋረጥ ከፍተኛ ፍላጎት ያለ እንደሆነ እንድናምን ስላደረገን በእኛም በኩል ይህንን በአጽንኦት እንድንመለከተው አስገድዶናል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ ውል ተፈራርመን መስራት ሲገባን በድርጅታቸሁ አሰራር መሰረት ያለፈውን አንድ ዓመት ያለ ውል መስራታችን ይታወቃል ፡፡ ከአሁን በኋላ ግን በእዚህ አሰራር መቀጠል አንችልም ፡፡ ስለሆነም ከስፖንሰሮቻችን ጋር እስከ ሲዝን 4 የመጨረሻ 13ኛ ክፍል ድረስ የተደረገውን ውል ከግምት ውስጥ በማስገባት እስከ ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ፕሮግራማችን በጣቢያቸሁ እንዲተላለፍ በእኛ በኩል አስቀድመን ዝግጅታችንን የጨረስን መሆናችንን እያሳወቅን፤ ከግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በጣቢያቸሁ ሲተላለፍ የነበረው “ጆሲ ኢን ዘ ሃውስ ሾው” የተሰኘው ፕሮግራማችን በእናተው አስገዳጅነትና ተገቢ ያልሆነ አሰራር እንደምናቋርጥ አስቀድመን እናሳውቃለን ፡፡

ከሰላምታጋር