Monday 21 October 2019

"ለውጡ ሐዲዱን ስቷል ብዬ ነው የማምነው" አርቲስት ታማኝ በየነ

ታማኝ በየነ ዘርፈ ብዙ የኪነ ጥበብ ባለሙያ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ፖለቲከኛ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ፣ ኮሜዲያን እንደሆነ ይነገርለታል። ታማኝ በአገሪቷ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በስደት ወደ አሜሪካ አቅንቶ ለበርካታ ዓመታት የመንግሥትን አስተዳዳር ሲተች፣ ሲቃወም ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከ22 ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ ታማኝ የአገሩን ምድር መርገጡ ይታወሳል። ለውጡን በመደገፍም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል።
በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ የኢሬቻ በዓል ሲከበር የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ አርቲስት ታማኝ በየነ በፌስቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረው ሃሳብ የተነሳ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። 

አንዳንዶች 'ተደምሮ ነበር ተቀነሰ' የሚሉ አስተያየቶችንም ሰንዝረዋል። ቢቢሲም ይህንና ሌሎች የአገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካን አስመልክቶ ከታማኝ በየነ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ሰዎች ፖለቲከኛ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ጋዜጠኛ፣ አርቲስት ይሉሃል። አንተ ራስህን የምታስቀምጠው የትኛው ላይ ነው?
እኔ መቼም ራሴን የምገልፀው በኪነጥበብ ውስጥ ነው፤ ግን ሁኔታዎች ገፉ ገፉና ወደ ፖለቲካ መድረኩ አመጡኝ እንጅ የሕይወቴ መነሻውም ገና የሰባት የስምንት ዓመት ልጅ ሆኜ ሙዚቃ ነው ሕይወቴ።
በእርግጥ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ከኪነ ጥበቡ እየራቅኩ ሄድኩ እንጂ አሁንም ራሴን የማየው የጥበብ ሰው አድርጌ ነው። በእርግጥ ሰዎች የሰጡኝ የተለያዩ ማዕረጎች አሉ፤ ግን ራሴን እንደዛ አድርጌ አልገልፀውም።
ወደ ኢትዮጵያ መጥተህ ከተመለስክ በኋላ ብዙም ድምፅህ አልተሰማም። አሁን ምን እየሠራህ ነው?
እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ በግል ብዙ ይመጣልኛል።
ሁለት ጊዜ ነው ወደ ኢትዮጵያ የሄድኩት። የመጀመሪያው ወደ አገራችሁ ግቡ ሲባል ነው የሄድኩት። 27 ቀን ገደማ ነው የቆየሁት። ያንንም በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወርኩ ሥራ ላይ ነው ያሳለፍኩት። በዚያ ጊዜም የተፈጠሩ ችግሮች ነበሩ - የቡራዩ። እርዳታ ለማሰባሰብ ጥረት አድርጌ ነው ወደ አሜሪካ የተመለስኩት።
ተመልሼ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ ደግሞ የጌዲዮና ጉጂ ችግር ተፈጠረ። በዚያ ምክንያት እርዳታ ሳሰባስብ ነበር። እሱ እንዳለቀ ከአሜሪካው ግብረ ሰናይ ድርጅት ወርልድ ቪዥን ጋር በመሆን እርዳታውን ለማድረስ ተመለስኩ።
እዚያም ሄጀ በተለያዩ አካባቢዎች ችግር ለደረሰባቸው ወገኖች እርዳታ ሳደርስ ነበር። የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ ነበርኩ። እንግዲህ ይህን አድርጌ የተመለስኩት ሰኔ መጀመሪያ ላይ ነው። ጠፋህ የምባለውም ለአራት ወር ያህል ነው። ይሄ አራት ወር ደግሞ በጣም ፈተና ውስጥ ያለፍኩበት ጊዜ ነው።
በጣም በቅርብ የማውቃቸው ዶክተር አምባቸውና የሌሎቹም በዚያ መልክ ሕይወታቸውን ያጡት የአማራ ክልል ባለሥልጣኖች ሞት ለእኔ እንደ ሰው በጣም ከባድ ሃዘን ነበር። እንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ በአካባቢው የፈጠረው የፖለቲካ ትርምስም ቀላል አልነበረም።
ከዚያ እንደገና በኢሳት ጊዜያዊ ኃላፊነት ላይ ነበርኩና በውስጡ የተፈጠረውን ችግር ለማርገብ ብዙ ጥረት አድርጌ ነበር። ስመለስ ሁኔታዎች እንደጠበቅኳቸው አልሆኑም። በዚያ ምክንያት እንግዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ዛሬ የምናገረው፤ ኃላፊነቴን ለቅቄ ወጥቻለሁ።
በዚህ ምክንያት ተደራራቢ የሆኑ የመንፈስም፤ የስሜት መጎዳትም ደርሶብኛል። ምክንያቱም ያን ሚዲያ በእግሩ ካቆሙት ውስጥ አንዱ ነኝ። ስድስት ዓመት በሙሉ አንድም የእረፍት ቀን ቤቴ አሳልፌ አላውቅም፤ ልጆቼን በአግባቡ በእረፍት ቀን አይቻቸው አላውቅም።
ለስድስት ዓመታት ዓለምን እየዞርኩ፤ እየለመንኩም [በዚህ ቋንቋ መናገር እችላለሁ] ያቋቋምኩት ድርጅት ፊቴ ላይ እንደዚህ ዓይነት ችግር ሲገጥመው በጣም ተጎድቼ ነበር እና ኃላፊነቴንም ለቅቄያለሁ።
በራስህ ፈቃድ ነው የለቀቅከው?
አዎ በራሴ ፈቃድ ነው የለቀቅኩት። እንደማይሆን ሳውቅ መልቀቅ ነበረብኝ። ሌላ ተጨማሪ ጉዳት፣ ሌላ ጭቅጭቅ፣ ሌላ ውዝግብ ላለመፍጠር ስል ነው በዝምታ እስካሁን ድረስ የቆየሁት።
አገር ቤት ከመግባታችን በፊት በየጊዜው በአገሪቱ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ በኢሳት ላይ እየወጣሁ ሃሳቤን እገልፃለሁ፣ እከራከራለሁ፣ መረጃዎችን አቀርባለሁ። በተጨማሪም በየቦታው ሄጀ በምናገራቸው ንግግሮች በየጊዜው ሃሳቤን ስለምገልፅ ያ በመቋረጡ ምክንያት ነው ብዙ ሰው ጠፋህ የሚለው።
እኔ አሁንም በአገሬ ጉዳይ ላይ አቅሜ የሚችለውን እያደረኩ ነው ያለሁት። ምንም የተደበቅኩበት፤ የጠፋሁበት ምክንያት የለም።
አሁንም ስለ አገርህ የሚሰማህ ስሜት ይኖራል ብ አስባለሁሃሳቤን የምገልፅበት መንገድ አጣሁ ብለህ ታስባለህ?
አጣሁ ማለት አልችልም። ለምን አጣለሁ? ግን እንደበፊቱ . . . አየሽ እዚያው ነው የምሠራው፤ አዳሬ ኑሮዬ ማለት ነው። የተፈጠሩ ሁኔታዎችን በየቀኑ በኢሳት ስለምናገር ነው። አጣሁ ለማለት አልችልም። ይሄን ግን በሌላ በኩል እየሄድኩም እባካችሁ አነጋግሩኝ አልልም።
እኔ መፃፍ አልችልም፤ ተፈጥሮዬም አይደለም፤ ስሜቴንም አይገልፅልኝም። ግን በሚዲያ ደረጃ በዚህ ሃሳብ፣ በዚህ ጉዳይ. . . ያለኝ ማንም የለም። ስለዚህ በዚያ ምክንያት አልታየሁም እንጅ በየቀኑ የሚለዋወጠውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተደብቄ አይደለም ያለሁት።
አሁን ደግሞ አንዳንድ ችግሮች ሲፈጠሩ፤ ተከፍቶ በነበረው በር እየገባሁ ለምን ይሄ ሆነ? እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ? የሚል ጥያቄ አቀርብ ነበር። እስካሁን እሱም አልተዘጋም ነበር ለማለት ነው።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስተዳደር መምጣት በኋላ ያለውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ትመለከተዋለህ?
እንግዲህ ለውጥ መጥቷል ብሎ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እ . . . የዛሬ ዓመቱን ሙቀት መለኪያ ባይኖረንም በእርቅና መቻቻል፤ ያለፈውን በመተው ወደፊት ለመራመድ፤ አብሮ ለመጓዝ የሚሉት ሃሳቦች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተቀብሎት ነበር ማለት እችላለሁ። ሁሉም የሚለው ባያስማማን እንኳን 90 በመቶ ብንል ለእውነት የቀረብን ይመስለኛል።
ዶክተር ዐብይ ለዘመናት የሄድንበትን የመበቃቀል ስህተት 'በአዲስ መንፈስ በይቅርታ እንሻገር' ሲል እንደማንኛውም ዜጋ እኔም ደስ ብሎኝ ይሄን ሃሳብ ተቀብያለሁ። ይሄ እንግዲህ የሚሆነው 'ኢትዮጵያ የሄደችበትን የመከራ ዘመን በማሰብ አንድ ቦታ ላይ እንዘጋዋለን' የሚል እንደ አንድ ዜጋ እምነት ስለነበረኝ ነው።
አሁን ያሉትን ሁኔታዎች ስንመለከት በብሔር ተኮር ፖለቲካ ያሉ ኃይሎች ጫፍ እየወጡ ኢትዮጵያዊ የሚለውን የዜግነት ሃሳብ እየገፉ፤ ዜጎች እንደልባቸው እንደ ዜጋ የሚኖሩበትን እያፈረሱ የመገፋፋትና የማፈናቀል. . . እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይህ ሊታረም የሚችልበትን መንገድ እንደ አንድ ዜጋ በግሌ ሞክሬያለሁ ሊሰሙኝ የሚችሉ ባለሥልጣናትን ምን እያደረጋችሁ ነው? ብዬ ጮኼያለሁ፤ አዝናለሁ ይህን ስናገር ግን ተስፋ ሰጪ አይደለም። ያሰብነው ጋር እየሄድን አይደለም። ለውጡ ሐዲዱን ስቷል ብዬ ነው የማምነው።
ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ ሥልጣን ሲረከቡ የገቧቸውን ቃል እየፈፀሙ አይደለም ብለህ ነው የምታስበው?
መሬት ላይ ባለው ሁኔታ አዎ! ምክንያቱም ዶክተር ዐብይ በኢትዮጵያ ውስጥ አዎንታዊ፤ በተለይ የእናቶችን እንባ የሚጠርግ መንፈስና ሃሳብ ይዞ መጥቷል ብዬ ነው የማምነው፤ የተቀበልኩትም እንደዛ ነው።
አሁን ግን አክራሪ ብሔረተኞች የፈለጉትን የሚያደርጉበት፣ ዜጎች እንደ ዜጋ በነፃነት ሊንቀሳቀሱ የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ሲደርሱ ዶክተር ዐብይ ያላቸውን ሥልጣን እና አቅም ተጠቅመው የማስቆም ሥራ እየሠሩ አይደለም።
ይሄ ደግሞ አገሪቷን ወደ ከፋ ደረጃ ይገፋታል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ በእንዲህ ዓይነት ምስቅልቅል ሕይወት ውስጥ ነው ያለችው-አገሪቷ።
ትናንት በሙሉ ልብ ሁላችንም ለመደገፍ የቆምነውን ያህል አሁን አብሮ ለመቆም አስቸጋሪ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው ምን ተሰማህ?
ዶክተር ዐብይ የሠላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆኑ ሲባል እኔም እንደ ዜጋ፤ አገሬ በዚያ ክብር ላይ በመጠራቷ ደስ ብሎኝ 'እንኳን ደስ አለዎት' ብያለሁ።
24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ በዜግነት የሚንቀሳቀሱ ዜጎች 'በአገራችን እኩል ድምፅ የለንም' ብለው ተቃውሞ ለማሰማት ሲንቀሳቀሱ፤ ሲከለከሉና ሲታሰሩ፤ በሌላ በኩል እርሳችውን የሚደግፉ ደግሞ በይፋ . . . ይሄ በፍፁም በፍፁም ሊያኗኑረን የሚችል አይደለምና መስመር ስቷል።
ዶክተር ዐብይ እንደገና ቁጭ ብለው አይተው፣ አስበው፤ ለውጡን በምን መልኩ ላካሂድ የሚለውን ከሁሉም የኢትዮጵያ ባለድርሻዎች ጋር መምከር ካልቻሉ በስተቀር ስለኢትዮጵያ ሁኔታ አሁን በተመለከተ መጥፎ ዕይታ ነው ያለኝ።

ለውጡ አቅጣጫውን ሲስት ስለተመለከትክ የተለያዩ ጥረቶችን እንዳደረክ ነግረኸኛል። ምን ድረስ ነው ጥረት ያደረከው?
ይሄን ነገር መናገር አይከብድም ብለሽ ነው? መቼም በጣም ጥሬያለሁ ብዬ አስባለሁ። እውነቴን ነው የምልሽ ከእርሳቸው ጀምሮ ወደ ታች እስካሉት ባለሥልጣናት ድረስ ምንድን ነው ይሄ ነገር? እያልኩ ጮኼያለሁ፤ በሌላ በኩል ዝም አልክ የሚለኝ ሰው ቢኖርም፤ ዝም ግን አላልኩም። በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ለመናገር ሞክሬያለሁ።
አንዳንዴ ተመቸንም ብለን፣ ሁኔታው ስለፈቀደልንም፤ በውጭ ስለምንኖርም በማህበራዊ ሚዲያ የምንሰጣቸው አስተያየቶች አልፈው ሄደው በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ የተረዳንም አይመስለኝም እና ብዙ ውጥንቅጡ የጠፋበት አሠራር ነው ያለው። ይሄ መታረም አለበት።
በፍትህ ሥርዓቱ ትናንት ያለቀስነውን ያህል ዛሬም የ28 ቀን ቀጠሮ፣ የ18 ቀን ቀጠሮ እየተባለ ዜጎች እንደዛ ሲሰቃዩ ማየት ከዚህ በኋላ እንዲቀጥል እኔ እድል አልሰጥም።
ጠቅላይ ሚነስትሩ ምን ማድረግ አለባቸው ነው የምትለው?
በኢትዮጵያዊ መንፈስ እንደ አንድ አገር ዜጎች አብረን እንኖራለን፤ በመከባበር፣ በመፈቃቀድ እና ቂምን በመተው ይሄን መንፈስ ሲያነሱ በአብዛኛው የተቀበላቸው እኮ የዜግነት ፖለቲካን የሚደግፉ ወይም ደግሞ በኢትዮጵያዊነት የሚያምነው ኃይል ነው። ያን ኃይል ይዘው አገሪቷን መስመር ማስያዝ ነበረባቸው ብዬ አምናለሁ።
ያ ኃይል አሁን ተገፍቷል። ድምፅ የለውም። ለኢትዮጵያዊነት መብት መታገል የሚያስበው ኃይል የለም። አሁን በብሔር የተደራጁ ኃይሎች ናቸው እንደ ልብ የሚንቀሳቀሱት። ከእሱ ነው የሚጀምረው።
ስለዚህ ኢትዮጵያዊው ኃይል ለእርሳቸው ትልቁ ኃይላቸው መሆን ነበረበት። እሱን የተዉት ነው የሚመስለኝ። በሂደት ይታረማሉ ብዬ የማስባቸው ነገሮች ነበሩ ግን እየታረሙ አይደሉም።
ሕገ መንግሥቱስ ለምንድን ነው ድምፅ እንዲሰጥበት የማይደረገው? በዚህ ዓይነት ሕገ መንግሥት ልንፈርስ በየቦታው ጠመንጃ መወልወል በተጀመረበት አገር እንደ አገር መቀጠል አይቻልም። የሕዝቡን ድምፅ እየሰሙ አይመስለኝም። እየሰሙ ያሉት የብሔርተኞችን ነው።
በመሆኑም በሕገ መንግሥቱና ልዩ ኃይል በሚባለው ላይ ጠንከር ያለ አቋም ይዘው ካልወጡ በስተቀር፤ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ኢትዮጵያን የመምራቱ ነገር አደጋ ውስጥ ይገባል ብዬ ነው የማስበው።
በዚህ ዓመት ደግሞ ምርጫ ይጠበቃልአሁን ባለው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ምርጫ ይካሄዳል መባሉን እንዴት ነው የምታየው?
እኔን የሚታየኝ? ባለፈው ሳምንት ውስጥ ከአማራ ክልል የሚመጣ መኪና አዲስ አበባ መግባት የለበትም ተብሎ ወጣቶች መንገድ ዘግተው አትገቡም በሚሉበት፤ በምን ዓይነት መለኪያ ነው በዚያ ክልል ውስጥ እኔ የምፈልገው ሰው ይመረጣል ብዬ የማስበው። በፍፁም ሊሆን አይችልም።
በነፃነት የምትንቀሳቀሽበት አገር አይደለም፤ ከዚያ ብሔር ውጪ ከሆንሽ ነፃነት የለሽም። ዜጎችን በሁለት ዓይነት የሚከፍል - ልዩ ዜጋና መጤ ዜጋ በምንባባልበት. . . ምርጫ ተካሂዶ ዴሞክራሲ ይሰፍናል የሚል ቅዠት የለኝም። በፍፁም ሊሳካ የሚችል አይደለም። ብሔርተኞቹ አንድ ላይ መጥተው በበለጠ አደጋ የሚፈጥሩበት ምርጫ ነው የሚሆነው ብየ ነው የማስበው።
እንኳን ምርጫ ማካሄድ ሕግ ማስከበር ይቻላል ወይ? በሕግ የሚፈለጉ ሰዎች ወደ ክልላቸው ሄደው ከተደበቁ እኮ ማውጣት አይቻልም። በምን ዓይነት ዘዴ ነው ምርጫ የሚካሄደው። እንደዚህ ዓይነት ሕግ ባለበት ምን ዓይነት ምርጫ እንደሚካሄድ አይገባኝም። የሕግ የበላይነት ሲባል ዝም ብሎ አይደለም። መንግሥት ሕግ የማስፈፀም አቅም አለው ወይ? የሚለው ነው መታየት ያለበት።
እና ለውጡን በመደገፍህ ትቆጫለህ?
በፍፁም! ለምን እቆጫለሁ? ምክንያቱም ከማንም በቀረበ ኢትዮጵያ እስር ቤቶች ሲፈፀሙ የነበሩ ግፎችን ከተጎጂዎቹ አንደበት፣ ከተጎጅዎቹ ቤተሰቦች የተካፈልኩ ሰው ነኝ። ዛሬ እነዚያ ተጎጅዎች መፈታታቸው ለእኔ ትልቅ ነገር ነው።
በሌላ በኩል ይነስም ይብዛም፤ በምንፈልገው መልኩ ባይሄድም፤ ዛሬ ሃሳብ መግለፅ የሚቻልባቸው ሚዲያዎች ተከፍተው እያየን ነው። ስለዚህ ለውጡን ብንገፋበትና አጠንክረን ብንሄድ የተሻለ አገር፣ የተሻለ ቦታ መድረስ ስንችል እንደዚህ ወደ ኋላ በመጎተታችን ከመቆጨት በስተቀር ለውጡን በመደገፌ ለአንድ ደቂቃም አልፀፀትም።
ይህን ቃለ ምልልስ እንድናደርግ መነሻ የሆነ፤ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት በኢሬቻ በዓል ላይ አደረጉት የተባለውን ንግግር ተከትሎ በአንተ ስም ፌስቡክ ላይ የሰፈረው መልዕክት የአንተ ነው?
አዎ!
ብዙ ጊዜ አንተ የምትታወቀው ኢትዮጵያዊነትና ሰብዓዊነት በማቀንቀን ነው እና በዚህ መልዕክትህ ለአንድ ብሔር ወገነ፤ 'ተደምሮ ነበር ተቀነሰ' የሚሉ ሃሳቦች ተነስተዋል። 'እንደራጅ' ስትል ምን ማለትህ ነው?
ትክክለኛ ጥያቄ ነው። እኔ እንደራጅ ስል አሁንም ተበታትኖ የሚታየው ስለኢትዮጵያ ግድ የሚሰጠውን ኃይል ነው። እንደ ዜጋ በኢትዮጵያ ውስጥ በእኩልነት መኖር እንችላለን የሚለው ኃይል እየተገፋ ስላለ፤ እየለመንን አይሆንም ተደራጅተን ኢትዮጵያዊነታችንን ማስከበር አለብን የሚል ነው።
ነገር ግን ከኦሮሚያው ፕሬዚደንት ንግግር ጋር ተያይዞ አብረው የተነሱ ነገሮች አሉ። በዚህ በለውጥ ሂደቱ ውስጥ ትልቁ ነገር፤ ትናንትን ይቅር ብለን ወደፊት ለመራመድ ስለተነሳን እንጅ አንድን ሕዝብም ሆነ አንድን ግለሰብ በማጥቃት፣ በጠላትነት በመፈረጅ በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ በምንም መለኪያ ቁጭ ብዬ ላየው አልችልም።
ስለዚህ የተደረገው ነገር ስህተት ነው። ማንም ሆነ ማን 'ሰብረናቸዋል . . . እንዲህ አድርገናቸዋል' የሚል የዛቻና የበቀል መንፈስ ያለው ሃሳብ እንኳን የመንግሥት ባለሥልጣን ተራ ዜጋ ሊያደርገው የማይገባ ነው። አንዱ ባለጊዜ ነኝ ብሎ ሰብሬህ እንዲህ አድርጌ የሚል ከሆነ ለማንም አይጠቅምም። ለመጠፋፋት እንዘጋጅ እንደ ማለት ነው።
በሌላ በኩል ከአማራነት ጋር አያይዘውታል። ግን አማራስ ቢሆን . . . በማንም ሕዝብ ላይ እንዲህ ዓይነት በጅምላ ያነጣጠረ ነገር፤ በማንኛውም ጊዜ የፈለጉትን ነገር ሊሉኝ ይችላሉ ግን እቃወማለሁ። ኢትዮጵያዊ ዜጋ መብቱ ሲገፈፍ አሁንም ቆሜ አላይም።
እንደራጅም ስል 'ኢትዮጵያዊያን' ስላልተደራጁ ነው። የተደራጁት እንዲህ ዓይነት የበቀል ፖለቲካ እያራመዱ ነው የሚሄዱት። አሁንም ተበትኖ ያለው ኢትዮጵያዊ ኃይል እንዲደራጅ እፈልጋለሁ።
በአገሪቱ ውስጥ እየታ ያሉትን ነገሮች በመመልከት አንዳንዶች የከፋ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። አንተስ ይሄንን ስጋት ትጋራዋለህ?
ለሕዝቡ ማመላከት ያለብን ነገር በጎውን ስለሆነ ይህንን ጨለማውን ነገር ባልናገረው እመርጥ ነበር- ሟርት የሚባለው ዓይነት ስለሆነ።
ነገር ግን ወደ እውነቱ እየተጠጋን ከሄድን፤ በጣም እውር የሚያደርግ፣ የሚያሰክር የአልኮል መጠኑ የማይታወቅ ነው - ብሔርተኝነት፤ ምንም ጥያቄ የለውም ወደዚያ ሊወስደን ይችላል። አሁንም ጫፍ ጫፉን እያየን ነው።
አክራሪ ብሔርተኛ ሲኮን ማሰቢያ አዕምሮን ለሌላ አከራይቶ . . . በቃ ያ ሰው በሚያዘው መንገድ እየሄዱ . . . ግደል ያሉትን መግደል፤ አፍርስ ያሉትን ማፍረስ ነው። እንደ ሰው ቁጭ ብሎ አስቦ በራስ አዕምሮ መከራከር አይኖርምና እኔ አሁን አሁን ያሰጋኛል።
ኢትዮጵያዊያን በጋብቻም በማህበራዊ ሕይወትም የተቆራኙ ናቸው እየተባለ ይነገራል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የብሔር ግጭት ይባላል። ምንድን ነው ምክንያቱ ትላለህ?
ፖለቲከኞች ናቸው። በጣም ራስ ወዳድ የሆኑ፣ ከራሳቸው በላይ ማየት የማይፈልጉ፣ ከራስ ክብርና ጥቅም በላይ ማየት የማይፈልጉ ፖለቲከኞች እየገፉት ነው እንጂ ሕዝቡ ውስጥ አሁንም አብሮ መኖሩ ገና አልጠፋም።
ያ መተሳሰብ፣ መከባበር አሁንም አለ። ያ ባለበት እንዲዘልቅ ውሃ የሚያጠጣው፣ የሚንከባከበው ግን የለም። የሚያጠፋውን መንገድ እየገፉበት ነው ያለው።
ቁጠሩ ቢባል እንኳን ሁለት ሺህ የማይሞሉ ፖለቲከኞች ናቸው እኮ ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሆነውን ሕዝብ የሚያምሱት። ኃላፊነት የጎደለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምም ለሚደርሰው ውጥንቅጥ ምክንያት ነው። ትልቅ ኃላፊነት በሁሉም ዜጋ ላይ ነው ያለው።
ስለዚህ አሁን በምታያቸው ነገሮች ወደ ተቃውሞ ልትገባ ትችላለህ?
እንዴ?! በደንብ! እንደ በፊቱ በየኤምባሲው አልጮህም። መደረግ ያለበትን ሠርቶ ማድረግ ነው ብዬ ነው የማምነው እንጂ መቃወሜማ አይቀርም። በዚህ ዓይነት መቀጠል አንችልማ! እና በመሰባሰብ፣ ሥራ በመሥራት፣ በመደራጀት፣ መብታችንን ማስከበር በሚለው በጣም አምናለሁ።
የምትደግፈው የፖለቲካ ፓርቲ አለ?
አሁንማ የት አለ [ሳቅ] ቢኖር ኖሮ እኔስ መች እንደዚህ መከራዬን አይ ነበር። ችግሩ እኮ ያ ነው። ምንም እኮ ድምፃችንን ሊያሰማልን የቻለ ኃይል ባለመኖሩ እኮ ነው የተበተነው።
ሌላኛው የማነሳልህ ትረስት ፈንዱን በተመለከተ ነው። ትረስት ፈንዱ ላይ ያለህ ሚና ምንድን ነው?
በመጀመሪያ እንደተቋቋመ፤ እናንተ እንደዚህ ማድረግ ትችላላችሁ ሲባል፤ የደፈረሰ ውሃ የሚጠጣን ወገን ንፁህ ውሃ ማጠጣት ለእኛ በጣም ቀላል ነው። በጣም! ግን ከ5 ሚሊዮን እኮ አላለፍንም። በዚያው ጭቅጭቅ ጀመርን እና አንዳንዶች ገንዘባችን ለመንግሥት ሄዶ ምናምን እያሉ ይጠይቁኛል፤ ግን ለመንግሥት አልሄደም፤ መንግሥት ከፈለገ መዝረፍ የሚችለው በጣም በቂ ገንዘብ አለው። ያ አምስት ሚሊዮን መጣ አልመጣ. . . ኢትዮጵያ እኮ መርከብና አውሮፕላን የሚጠፉባት አገር ናት።
ከገንዘቡ በላይ ሕብረተሰቡን አንድ ላይ የማምጣት፣ ኃላፊነት መስጠት፣ ባለ ጉዳይ ነኝ እንዲል የማድረግ ነገር ነበር የነበረው። አጭር ማስታወቂያ ሠርቻለሁ። ነገር ግን ብዙም አልተሳተፍኩም።
ለምን?
እሱ እንኳን በሥራ መብዛት ምክንያት ነበር እንጅ በመጥፎ አልነበረም። ግን አሁንም በኅብረተሰቡ መካከል የተፈጠረውን የተበታተነ መንፈስ፤ ዶክተር ዐብይ እንዴት እንደሚያስተካክሉት አላውቅም። ካላስተካከሉት ብዙ ውጤታማ ይሆናል ብዬ አላስብም።
በዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ [ Global alliance] በተለይ ከምዕራብ ጉጂ ለተፈናቀሉት እርዳታ ስታሰባስብ ነበር። የትብብሩም ሊቀመንበር ነህ አሁን ምን እየሠራችሁ ነው?
በጌዲዮ ጉጂ ዞን ተፈናቅለው ለነበሩት ቤቶች አሠርተናል። ያ እንዳለቀ በይፋ ይመረቃል። ከዚህ በፊት የሠራናቸው ብዙ ሥራዎች አሉ። በቀደመው ሥርዓት ከእኛ ጋር መገናኘትና ስልክ መደዋወል ክልክል ስለነበር በጣም በጥንቃቄ የዜጎችን መብት ለማስከበር በርካታ ነገር እናደርግ ነበር።
የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ማሳከም፣ ልጆቻቸውን ላጡ ማቋቋሚያ መስጠት፣ ጋዜጠኞች ሲሰደዱ ለእነሱ ድጋፍ ማድረግ ብዙ ሥራ ሠርተናል። አሁን ምን እናድረግ? በሚለው ላይ ለመነጋገር በሚቀጥለው ወር ላይ ጉባዔ አለን። በኢትዮጵያም ተመዝግበን ለመንቀሳቀስ እየሠራን ነው።
እንድንቋቋም መነሻ የሆነን በሳዑዲ በዜጎች ላይ የደረሰው በደል ነበር። አሁን ላይ ጊዜያዊ እርዳታ እየሰጠን መቀጠል እንችላለን ወይ? የሚለውን በደንብ አጥንተን መተዳደሪያ ደንባችንን አስተካክለን ለመንቀሳቀስ እሞከርን ነው።



Friday 11 October 2019

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ ር አብይ አህመድ አሊ የአለም የሰላም ሽልማት አሽናፊ ሆነዋል


ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ፻ኛው የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ ሆኑ ለምድራችን እና ለሰው ልጆች ለሰላም ደህንነት ላደርጉት ታላቅ አስተዋፆ የሚሰጥው ይህ ታላቅ ሽልማት የመላው ኢትዮጵያውያን ጭምር በመሆኑ ደስታችን የላቀ ነው፡፡
እግዚአብሄር መልካሙን አድርጓል እና ደስ ብሎናል፡፡

እንኳን ደስ አላችሁ
እንኳን ደስ አለን