Sunday 12 July 2015

"ሰው ብቻ አትሁኑ"

"ሰው ብቻ አትሁኑ"
መጋቤ ሐዲስ እሸቱ

"ሰው ብቻ አትሁኑ...ሰው ብቻ ማለት ምንድን ማለት ነው? ብዬ ሳስብ፤ የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ በሚለብሰው ልብስ፣ በሚነዳው መኪና የኑሮን ስኬት የሚለካ ማለት ነው።
እስከ ሞት የሚኖር ማለት ነው፦ እንደ እንስሳ።

"...ታላቁ ሊቅ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል 'ሰው እግዚአብሔር ሲለየው' ይላል። ሰው እግዚአብሔር ሲለየው፤ ጠባዩ እንደ አራዊት፤ አመጋገቡ እንደ እንስሳ፣ ሆኖ መልኩ ብቻ የእግዚአብሔር ሆኖ ይቀራል። በጣም ቀለል ባለ አገላለጽ ሲም ካርዱ የወጣ ሞባይል(mobile ) ማለት ነው ። ጥሪ የማይቀበል፤ ለጉትቻ ማንጠልጠያ ብቻ የተሰራም ጆሮ አለ።"


"...እኔ በዕውነቱ ከተማው ፈርሶ እየተሰራ ነው እየተባለ ዐይናማዎቹ ሲያወሩም ሲያስወሩም እሰማለው። ፈርሶ መሰራት ያለበት የሰዉ አስተሳሰብ ነው።... የሰዉ አስተሳሰብ ፈርሶ ካልተሰራ፤ የተሰራ ከተማ ይፈርሳል። ጃፓንና ቻይና ሀገራቸውን ያለሙት መጀመሪያ አስተሳሰባቸውን አልምተው ነው። አስተሳሰቡ ያልለማ ሕዝብ የለማውን ያወድማል።"
"ቤታችሁ ገብታችሁ እንድታጤኑት ነው። እነዛ... (ምንትስ) የምንላቸው ክርስቲያኖችን አርደዋል... ምዕራባውያኑ ደግሞ ክርስትናን እራሱን አርደውታል።....ወንድ ለወንድ፣ ሴት ለሴት፣ በቤተክርስቲያናቸው እያጋቡ፤ ክርስትናን አጋድመው ያረዱ ምዕራባውያን ናቸው። (ይህን ሁሉ ያመጣውም) የምዕራባውያን ልክ ያጣ ነጻነትና ገደብ ያለፈ ዝርክርክነት ነው።"
"እንደምታዩት እኔ ዐይነ ስውር ነኝ። ቀላል አይደለም.... እንክዋን ዘውትር ዓይን አጥቶ አንድ ቀን መብራት ሲሄድ ስንት እንደምታማርሩ ታውቅታላችሁ። አንድ ቀን ግን አልቅሼ አላውቅም። ከሞት ወዲያ መብራት አለ። ከመቃብር በላይ መብራት አለ። ... ወደ መቃብር ሲወርድ ማንም ዓይነ ስውር ነው። ማንም ዐይኑ እያየ የተቀበረ የለም። ተስፋችን ግን ምንድን ነው? ከሞት ወዲያ ሕይወት አለ። ከሞት ወዲያ ብርሃን አለ።"
"...አንድ አንድ ጊዜ እመኛለሁ። የማይረባ ነገር ስናይ (ዓይናችንን) የሚያጠፋ ቆጣሪ ቢኖር... መልካም ነገር እስክናይ ድረስ ለጊዜው የሚያጠፋ ቆጣሪ ቢኖር።
"አሁን እንደው ጆሮ በካርድ የሚሰራ ቢሆን ሐሜት እንሰማ ነበር?(ከፍተኛ ሳቅ)...
የምንፈልገውን (ብቻ) አውርተን ስዊች ኦፍ እናደርገው ነበር። ስንት ዞማ ጸጉር ይዞ አስተሳሰቡ የከረደደ አለ።
"ጀርመን ሀገር ሄጄ ሲነግሩኝ፤ ባለ አምስት ኮከብ የውሻ ሆቴል አለ ተባለ። እኛ ሀገር አምስት ኮከብ ሆቴል ገብተው የበሉ ትንሽ ዝና (ሀብት) እና ትንሽ ሥልጣን ያላቸው ናቸው። ማን ይገባል ከነሱ ውጪ። ግን ሰዋች ነን። የጀርመን ውሻ
ዛሬም ውሻ ነው ለዘላለምም ውሻ ነው። እኛ ግን ሰው ነን። እንደ ሰው አስቡ (ምዕመናን) በማርያም።"
"...የንጉሠ ነገሥቱ የክርስቶስ አልጋ ወራሾች ነን... የደስታችሁ ልኬት የደስታችሁ ሚዛን ምግብና መጠጥ አይሁን፤ መኪናና ቤት ዝናንም አታርጉ። እኛ መለኪያችን
ጽድቅ ነው። መከኪያችን መንግሥተ ሰማያት ነው። ያ የምንገባበት ቤት ደግም የተዋበ፣ የደመቀ፣ መብራት ውሀ የማይሄድበት፤ 24 ሰዓት ክርስቶስ የሚያበራበት፤ 24 ሰዓት የሕይወት ውሀ የሚጠጣበት፤ ሀብታም፤ ደሀ፣ ተራሰው የማይባልበት፣ እገሌ ግባ እገሌ ውጣ የማይባልበት ቦታ ነው።