Tuesday 30 October 2018

ዶ/ር ዓቢይ ከሥልጣን ይውረድ!


 ሙአዘ ጥበብ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አንድ ባልና ሚስት ነበሩ። ሴትየዋ ሙያ ሚባል ነገር አልፈጠረባትም። ሁልጊዜ ንፍሮ እየቀቀለች ነው ምታቀርበው። እሱም በጣም ከመልመዱ የተነሳ እንግዳ እንኳን ሲመጣ “እስቲ ያን እጅ ሚያስቆረጥም ንፍሮ ቀቅይላቸው” ነው ሚለው።
አንድ ቀን ታድያ ይቺ ሙያ የሌላት ሚስቱ ጥላው ትሄዳለች። እጅግ በጣም መጎዳቱን ያዩት ጎረቤቶቹ ሌላ ሚስት ያመጡለታል። እሷንም ባገባ በመጀመርያው ቀን የተለያየ አይነት ምግብ ሠርታ ቡፌ ደርድራ ታቀርባለች። ይሄ ምንድነው? ይላል በመደነቅ፤ እርሷም ምግብ ነዋ ትለዋለች። 

በጣም እየተገረመ “ለካ እንደዚህም አለ” እያለ እስኪጠግብ ከበላ በኋላ በሩን ዘግቶ በአለንጋ ይገርፋት ጀመር። ጩኸቷን የሰሙ ጎረቤቶች ተሯሩጠው ይመጡና “ምን ሆነሃል? ሚስት እንድትሆንህ እንጂ እንድትደበድባት አይደለም’ኮ ያጋባንህ!” ይሉታል።

እሱም “እስከዛሬ ድረስ በንፍሮ ስቀቀል የት ነበረች?” አለ ይባላል።
ብዙዎቻችን አዲስ ለውጥ የሬት ያህል ይመረናል። ቀድሞ የተጸናወተን የጠባብነት ባህል/አስተሳሰብ አዲሱን ለውጥ መሸከም እንዲከብደን ያደርገናል። በዚህም ጊዜ ራሳችንን ከለውጡ ጋር ለማጣጣም ከመጣር ይልቅ በለውጡና ለውጡን ያመጡ ሰዎች(ቡድኖች) ላይ የስድብ /የተቃውሞ/ ውርጅብኝ ማውረድ ይቀናናል።
በዶ/ር ዓቢይ አሕመድ ላይ የተከፈቱ አንዳንድ ዘመቻዎች ከዚህ የተለዩ አይደሉም። ባርነትን የለመደ ነፃነትን ከባርነት በላይ ይጸየፋልና ከለውጡ ጋር መራመድ ያቃታቸው በቁማቸው ያንቀላፉ አንዳንድ ብሔርተኞችና የቀድሞው ሥርዓት ልዩ ተጠቃሚዎች አፋቸውን ሞልተው “ዓቢይ ከሥልጣን ይውረድ” የሚል አሳፋሪ ዘመቻ መክፈታቸው አስገርሞኛል።
አያቶቻችን “ሞኝ እርሱ ባያፍር ዘመዱ ያፍር” የሚሉት ብሂል አለ። እናም በእነዚህ ሰዎች ሥራ እነርሱ ባያፍሩም እኛ ወገኖቻቸው እናፍራለን አፍረናልም። ኢትዮጵያም አፍራለች።
ሁሌም ስንራመድ እያስተዋልን ቢሆን ለእኛ መልካም ነው።

Thursday 25 October 2018

የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ ብሄር - ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ፣





Image result for Sahle work zewde Ethiopia president

የካቲት፣ 1942 አዲስ አበባ ውስጥ የተወለዱት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ እድገታቸውም እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡
ወ/ሮ ሳህለወርቅ የሁለት ወንድ ልጆች እናት ሲሆኑ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡
ከፈረንሳዩ ሞንተፔለ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ የተመረቁት ወ/ሮ ሳህለወርቅ እ.ጎ.አ ከ1989 እስከ 1993 ባሉት ዓመታት ተቀማጭነታቸውን ሴኒጋል ውስጥ በማድረግ የጊኒ ቢሳው፣ የጋምቢያ፣ የማሊ፣ የኬፕ ቨርድ እና የጊኒ አምባሳደር በመሆን ማገልገላቸውን ተመልክተናል፡፡
እ.ጎ.አ ከ1993-2002 በጅቡቲ አምባሳደር ሆነው ሰርተዋል፡፡ በዚሁ ወቅት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ቋሚ ተወካይም ነበሩ።
እ.ጎ.አ ከ2002-2006 በፈረንሳይ አምባሳደር እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ተወካይ ሆነው ሰርተዋል።
በመቀጠልም፣ በተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ ውስጥ የተቀናጀው የሰላም አስከባሪ ሃይል ተወካይ በመሆን በሴንትራል አፍሪካ(BINUCA) ኃላፊ በመሆን ማገልገላቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡
ወ/ሮ ሳህለወርቅ፣ በአፍሪካ ሕብረት እና በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ውስጥ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ በመሆን እንዲሁም በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥም የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው አገልግለዋል፡፡
እ.ጎ.አ በ2011 የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሃፊ የነበሩት ባንኪ ሙን፣ በኬኒያ የተባበሩት መንግሥታት ዳይሬክተር ጄነራል አድርገው ሾመዋቸው አገልግለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ በተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በአፍሪካ ሕብረት ልዩ ተወካይ እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት የተባበሩት መንግሥታት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመው እንደነበር ለማወቅ ችለናል፡፡
...
ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር፣ በሥራ ዘመናቸው ስለሰላም ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ የተናገሩት ርዕሰ ብሄሯ፣ “ሥር የሰደደውን ጥላቻ፣ መናናቅና አልፎ አልፎ የሚታየውን ጠብ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ በዳበረ የቤተ እምነቶች ጥበብና የሽምግልና ሥርዓት ከወዲሁ በመግታት ለራሳችንም ሆነ ለትውልድ የምታኮራ ሐገር መፍጠር ይኖርብናል” ሲሉ ተናግረዋል

Tuesday 16 October 2018

ትዳር ነጥብ ማስቆጠሪያ አይደለም፡

Dsniel Kibert
“ትዳር ነጥብ ማስቆጠሪያ አይደለም፡፡ ልምድ ማስቆጠሪያ እንጂ፡፡ ትዳር በሁሉም ነገር መግባባትን፣ መተማመንንና መስማማትን አይጠይቅም፤ ከተለያዩ በታዎች በመጡ፣ በጾታም በማይገናኙ ሁለት ሰዎች የሚመሠረት ነውና፡፡
ትዳር የተለያዩ ሰዎች ያዘጋጁዋቸው ሁለት ፈትሎች እየተገመዱ የሚሄዱበት ሽመና ነው፡፡ ሲጀመር ጫፍና ጫፉ ይያያዛል፣ በሂደት ግን ካልተገመደው የተገመደው እየበለጠ ይሄዳል፡፡ ግመዳው ግን እንዲህ በቀላሉ የሚከወን አይደለም፡፡”
ትዳርን የተቃናና የተሳካ ለማድረግ በሁለት ባላዎች ላይ መትከል ያሻል ይላሉ፤ ሊቃውንቱ፡፡ በመማርና በመማር፡፡ ሰው ሌላውን ሥራ ሁሉ የሚሠራው አንድም ተምሮ አንድም ለምዶ ነው፡፡ ትዳር ሲመሠርት ግን ትምህርትም ልምድም የለም፡፡
ትዳርን እንደ ትምህርት ዓይነት መርጦ፣ ከፊደል እስከ ዳዊት ደግሞ፤ አድርሶ አስመስክሮ የተመረቀ የለም፡፡እዚህም እዚያም ትዳርን የተመለከተ ንባብና ሐሳብ ይገኝ ካልሆነ የትዳር ዲፕሎማና ዲግሪ፣ ማስተርስና ዱክትርና የለም፡፡  ሌላውን ሞያ ለተግባሩ ተመሳሳይ በሆነ አምሳያ ተግባር(ዎርክ ሾፕ/ሲሙሌተር) ልምምድ ማድረግ ይቻላል፡፡
ትዳርን ግን በአምሳያው ላይ ልምምድ ማድረግ አይቻልም፡፡ ‹እገሌ ይህን ያህል ዓመት ትዳርን በተመለከተ ልምድ አለው› ብሎ መጻፍ የሚችል መሥሪያ ቤትም የለም፡፡ ለዚህ ነው በትዳር ጉዞ ውስጥ ‹መማር› ወሳኝ የሚሆነው፡፡  ትዳር ማለት ጥቂት ዕውቀትና ጥቂት ሐሳብ ይዘው ገብተው፣ እየኖሩ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ ስለ ዋና በሚገባ ማወቅ የሚቻለው እየዋኙ እንደሆነው ሁሉ፣ ስለ ትዳር በበቂ መማር የሚቻለው እየኖሩ ነው፡፡
ሁለቱም በተለያዩ ቤተሰቦች ባሕልና መርሕ ያደጉ፣ አንዱ ለሌላው ተብሎ በዕውቅ ያልተሠሩ፣ በነጠላ ተወልደው በድርብ የሚኖሩ ናቸውና፡፡ በትዳር መርከብ ውስጥ ከሌላው ጋር ሲኖሩ ሊከሰቱ የሚችሉትን የአስተሳሰብ፣ የፍላጎት፣ ጠባይና የአካሄድ ለውጦች አስቀድሞና አስረግጦ መተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡
እንኳን አንዱ ስለሌላው ስለራሱም ለውጥ ቀድሞ መተንበይ ይከብደዋል። ይባስ ብሎም ከዚያ በፊት ያልነበሩ ሦስት ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ በየራሳቸው ሲወስኑና ሲያደርጉ የኖሩት ወንድና ሴት በጋብቻ ምክንያት ሥልጣናቸው የጋራ፣ ኃላፊነታቸው የጋራ፣ ውሳኔያቸውም የጋራ ይሆናል።
መመካከር፣ መግባባትና መጋራት የግድ ይሆናል፡፡ በአንድ ዙፋን ሁለት ነገሥታት ይነግሣሉ፡፡ በእዝ ሠንሠለት ሁለት ሰዎች ለአንድ ሰው ተጠሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንድ ሰው ግን ለሁለት ሰው ተጠሪ አይሆንም፡፡ በትዳር ውስጥ ግን ይከሰታል፡፡ አንድ ልጅ፣ አንድ የቤት ሠራተኛ፣ አንድ በቤት ውስጥ የሚኖር ሰው ለሁለት ሰዎች ተጠሪ ይሆናል፡፡
በሁለቱ ጋብቻ ምክንያት ሌላ ማኅበረሰብ ይፈጠራል፡፡ ሲለጥቅ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የሚተቃቀፉ፣ አንዳንድ ጊዜም የሚገፋፉ ሁለት ቤተሰቦች ከሁለቱ ጀርባ ይመጣሉ፡፡ መጥተውም ወይ ጸጥ ያለ፣ አለያም ማዕበል የበዛበት ውቅያኖስ ይፈጥራሉ፡፡ ይህን የቤተሰብ ውቅያኖስ ማስተዳደር ለተጋቢዎቹ አዲስ ነገር ነው፡፡ ሲሠልስ ደግሞ ከሁለቱ ኑሮ ልጆች ይወለዳሉ፡፡
ይህን አዲስ የተፈጥሮ ስጦታ መቀበል፣ ተቀብሎም ማስተዳደር ዕውቀት፣ ብስለትና ጥበብ ይጠይቃል፡፡
በዚህ ሁሉ ጉዞ ውስጥ ብልህ ይማራል፣ ሞኝ ያማርራል፡፡ ብልህ ከምን ይማራል? ቢሉ ከሦስት ነገሮች ይማራል፡፡ ከራሱ ጉዞ ይማራል፤ ከትዳር አጋሩ ጉዞ ይማራል፤ ከሁለቱም ጉዞ ይማራል።

ቀድሞ የሚያውቃቸውን፣ ይሆናሉ ብሎ ሲገምታቸው የኖሩትን፣ እንዲሆኑ የሚፈልጋቸውንና እንዲያደርጋቸው የተመከረውን በትዳር ውስጥ ይሞክራቸዋል፡፡ የተሳካ ውጤት ካመጣለት፣ እሰየው ብሎ መመሪያው ያደርጋቸዋል፡፡ ችግር ከተፈጠረበት፣ ይቅርታ ብሎ ያርማቸዋል፡፡ እየተሞረደና እየተሳለ፣ እያወቀና እየበሰለ፣ እየታረመና እየተስተካከለ ይሄዳል፡፡
ለዚህም ነው የተሟላ ባል ማግኘት አይቻልም፤ የሚሟላ ባል እንጂ፣ የተሟላች ሚስትም ማግኘት ከባድ ነው፣ የምትሟላ ሚስት እንጂ የሚባለው፡፡ ብልህ ከትዳር አጋሩም ይማራል፡፡ የትዳር አጋርን በእጮኝነት ጊዜ ማየት ፀሐይን በሩቁ እንደማየት፣ በትዳር ጊዜ ማየት ደግሞ ፀሐይን ቀርቦ እንደማየት ነው ይባላል፡ አንዳንድ ጊዜ ከምናስበው የተለየ ነገር ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህ መሆኑን ቀድሜ ባውቅ ኖሮ አላገባትም/ አላገባውም ነበር ያሰኛል፡፡
ሊቃውንቱ ‹እንዳውቅህ ተገለጥ› ይላሉ፡፡ የአንድን ሰው ጠባይ፣ ሐሳብና አቋም መገለጡን አንጥላው፡፡ባወቅነው መጠን እንዴት መያዝ፣ እንዴትስ ማሸነፍ እንደምንችል እናውቃለንና፡፡ ከማያውቁት ነገር ጋር መኖር እንጂ ካወቁት ነገር ጋር መኖር አያስፈራም። ከትዳር አጋርህ ጋር ይበልጥ አብረሃት በኖርክ ቁጥር ይበልጥ ታውቃታለህ፤ ይበልጥ ባወቅካት ቁጥርም ይበልጥ አብረሃት ትኖራለህ፡፡
ብልህ ባል ከብርታቷም ሆነ ከድካሟ፣ ከትዕግሥቷም ሆነ ከንዴቷ፣ የሚወስደው ትምህርት አለ፡፡ ብልህ ሚስትም እንዲሁ፡፡ ትዳር ማለት ምርቃት የሌለበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ እንደ ጎበዝ የአብነት ተማሪ ሲቀጽሉ መኖር፡፡ አብረው መዝለቅ የቻሉ ባለትዳሮች በሚገባ እየተማሩ፣ የሰለጡ ባለትዳሮች ይሆናሉ፡፡
በትዳር መማር ብቻ ሳይሆን መማማርም አለ። ከየራሳቸውና ከአጋራቸው ብቻ ሳይሆን ከጋራ ኑሯቸውም ይማራሉ፡፡ ጋብቻ ማለት በትዳር ላይ ሥልጣንና ኃላፊነት የሚረከቡበት ቀን ነው፡፡  ጋብቻ በሰጣቸው ሥልጣን ብቻ የሚጠቀሙ ባለትዳሮች ፍቻቸው ቅርብ ነው፡፡ ጋብቻ በሰጣቸው ኃላፊነት ብቻ የሚጠቀሙ ባለትዳሮችም ምሬታቸው ቅርብ ነው፡፡ ጋብቻ ሥልጣንና ኃላፊነት ነው፡፡
ትዳር የሠመረ የሚሆነው እነዚህ ሁለቱ ሚዛን ሲሠሩ ነው። ትዳር ማለት የሥልጣንና የኃላፊነት አማካዩ ነው፡፡ኃላፊነት በተሞላበት ስሜት ሥልጣንን ለመጠቀምና ሥልጣን ባለው መንገድ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚችሉበትን ዘዴ የሚያገኙት አብሮ በመኖር አብሮም በመማማር ነው፡፡ እየተማማሩ በሄዱ ቁጥር ሥልጣናቸውን የጋራ፣ ኃላፊነታቸውንም የጋራ ያደርጉታል፡፡
ትዳርን የሚያቆመው ሌላው ባላ ደግሞ ‹መማር› ነው፡፡ ይቅር ማለት፡፡ ይቅር ማለት ‹ለይቅርታ የተዘጋጀ ልብ› ይፈልጋል፡፡ ይቅር ማለት ሽማግሌ ገብቶ፣ ዕርቅ ወርዶ ይቅርታ ሲጠየቅ ‹እሺ ይቅር ብያለሁ› ማለት አይደለም፡፡ ነገሮችን ለማለፍና ለማሳለፍ፣ ራስ ምክንያት ሰጥቶ ይቅር ብሎ ለማለፍ ዝግጁ መሆን ነው፡፡
ነገሮችን በክፋትና በተንኮል ከማየት ይልቅ ከልምድ እጥረት፣ ከጊዜያዊ ስሜት፣ከማይታወቁ መነሻዎችና ከድካም ሊመጡ እንደሚችሉ በመረዳት ቀድሞ ይቅር ማለት፡፡  ቀድሞ ይቅር የሚል ሰው መፍትሔው ላይ እንጂ ችግሩ ላይ አይቆዝምም፤ነገሩን ከመፍተል ይልቅ መፍትሔውን ይሸምናል፡፡
ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው› ብሎ ስለ ሰቃዮቹ ለምኗል፡፡ ሰቃዮቹ ‹የምናደርገውን ስለማናውቅ ይቅር በለን› አላሉትም፡፡ እርሱ ራሱ የቅድሚያ ምክንያት ሰጥቶ ‹የሚያደርጉትን አያውቁም› አለላቸው እንጂ፡፡ የይቅርታ ልብ ማለት ይህ ነው፡፡
በማናቸውም ጊዜና በማናቸውም ሁኔታ እያስተሠረዩ መጓዝ፡፡ ትዳር ነጥብ ማስቆጠሪያ አይደለም፡፡ ልምድ ማስቆጠሪያ እንጂ፡፡ ትዳር በሁሉም ነገር መግባባትን፣ መተማመንንና መስማማትን አይጠይቅም፤ ከተለያዩ በታዎች በመጡ፣ በጾታም በማይገናኙ ሁለት ሰዎች የሚመሠረት ነውና፡፡
ትዳር የተለያዩ ሰዎች ያዘጋጁዋቸው ሁለት ፈትሎች እየተገመዱ የሚሄዱበት ሽመና ነው፡፡ ሲጀመር ጫፍና ጫፉ ይያያዛል፣ በሂደት ግን ካልተገመደው የተገመደው እየበለጠ ይሄዳል፡፡ ግመዳው ግን እንዲህ በቀላሉ የሚከወን አይደለም፡፡ ውስጡ ሕመም አለው።
ያንን ሕመም መጀመሪያ ማከም፣ በኋላም ማዳን የሚቻለው በይቅርታ ነው፤ በመማር፡፡ ውይይቱና ክርክሩ እንኳን ውጤት የሚያመጣው በሁለቱም ልብ ውስጥ የይቅርታ ልብ ካለ ብቻ ነው፡፡ ውጤቱ መሸናነፍ ሳይሆን መተራረም ከሆነ፡፡ መማር ‹ይቅር ብያለሁ› ማለት አይደለም፡፡
መተውና መርሳት ጭምር እንጂ፡፡ ፋይል እየሰበሰቡና በትናንቱ እርሾ የዛሬውን ሊጥ እያቦኩ መሄድ አይደለም፡፡ በትዳር መጋገር ያለበት አፍለኛ እንጀራ ነው፡፡ ከትናንቱ ተምሮና ምሮ መሄድ እንጂ፣ አምርሮና አማርሮ መሄድ ትዳርን ይበክለዋል፡፡
መማርና መማር – ለተቃና ትዳር፡፡