Tuesday 30 October 2018

ዶ/ር ዓቢይ ከሥልጣን ይውረድ!


 ሙአዘ ጥበብ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አንድ ባልና ሚስት ነበሩ። ሴትየዋ ሙያ ሚባል ነገር አልፈጠረባትም። ሁልጊዜ ንፍሮ እየቀቀለች ነው ምታቀርበው። እሱም በጣም ከመልመዱ የተነሳ እንግዳ እንኳን ሲመጣ “እስቲ ያን እጅ ሚያስቆረጥም ንፍሮ ቀቅይላቸው” ነው ሚለው።
አንድ ቀን ታድያ ይቺ ሙያ የሌላት ሚስቱ ጥላው ትሄዳለች። እጅግ በጣም መጎዳቱን ያዩት ጎረቤቶቹ ሌላ ሚስት ያመጡለታል። እሷንም ባገባ በመጀመርያው ቀን የተለያየ አይነት ምግብ ሠርታ ቡፌ ደርድራ ታቀርባለች። ይሄ ምንድነው? ይላል በመደነቅ፤ እርሷም ምግብ ነዋ ትለዋለች። 

በጣም እየተገረመ “ለካ እንደዚህም አለ” እያለ እስኪጠግብ ከበላ በኋላ በሩን ዘግቶ በአለንጋ ይገርፋት ጀመር። ጩኸቷን የሰሙ ጎረቤቶች ተሯሩጠው ይመጡና “ምን ሆነሃል? ሚስት እንድትሆንህ እንጂ እንድትደበድባት አይደለም’ኮ ያጋባንህ!” ይሉታል።

እሱም “እስከዛሬ ድረስ በንፍሮ ስቀቀል የት ነበረች?” አለ ይባላል።
ብዙዎቻችን አዲስ ለውጥ የሬት ያህል ይመረናል። ቀድሞ የተጸናወተን የጠባብነት ባህል/አስተሳሰብ አዲሱን ለውጥ መሸከም እንዲከብደን ያደርገናል። በዚህም ጊዜ ራሳችንን ከለውጡ ጋር ለማጣጣም ከመጣር ይልቅ በለውጡና ለውጡን ያመጡ ሰዎች(ቡድኖች) ላይ የስድብ /የተቃውሞ/ ውርጅብኝ ማውረድ ይቀናናል።
በዶ/ር ዓቢይ አሕመድ ላይ የተከፈቱ አንዳንድ ዘመቻዎች ከዚህ የተለዩ አይደሉም። ባርነትን የለመደ ነፃነትን ከባርነት በላይ ይጸየፋልና ከለውጡ ጋር መራመድ ያቃታቸው በቁማቸው ያንቀላፉ አንዳንድ ብሔርተኞችና የቀድሞው ሥርዓት ልዩ ተጠቃሚዎች አፋቸውን ሞልተው “ዓቢይ ከሥልጣን ይውረድ” የሚል አሳፋሪ ዘመቻ መክፈታቸው አስገርሞኛል።
አያቶቻችን “ሞኝ እርሱ ባያፍር ዘመዱ ያፍር” የሚሉት ብሂል አለ። እናም በእነዚህ ሰዎች ሥራ እነርሱ ባያፍሩም እኛ ወገኖቻቸው እናፍራለን አፍረናልም። ኢትዮጵያም አፍራለች።
ሁሌም ስንራመድ እያስተዋልን ቢሆን ለእኛ መልካም ነው።

No comments:

Post a Comment