Sunday 7 July 2013

የግብረ ሰዶማውያኑ ኑዛዜ በኢትዮጵያ

‹‹አዲስ አበባ ውስጥ ግብረ ሰዶማዊነት ተስፋፍቷል፡፡ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በየመንደሩ፣ በየሥርቻው፣ በየጓዳውና ጉድጓዳው ራሳቸውን ደብቀው ያደፈጡ ሁሉ ቢቆጠሩ ብዛታችን ያደላል፡፡ መጠሪያ ስማችን ጌይ ወይም ግብረ ሰዶማዊ የሚል ሳይሆን ‘ዜጋ’ የሚለው ነው፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ያልገቡ ሌሎች ወገኖችን ደግሞ ‹‹ቀጥ›› በሚል እንጠራቸዋለን፡፡››

ይህንን የተናገሩት ከሰባት እስከ 32 ዓመት ድረስ ሕይወታቸውን በግብረ ሰዶማዊነት ያሳለፉት ግብረ ሰዶማውያንና ግብረ ሰዶማውያት (ወንዶችና ሴቶች)፣ ‹‹ዝምታው ይሰበር ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ዶክሜንተሪ ፊልም (ቪሲዲ) ውስጥ ባካሄዱት ቃለ መጠይቅ ላይ ነው፡፡

በቸርችል ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ‹‹ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም ግብረ ሰዶማዊነት በኢትዮጵያ የ666 አሠራር›› የሚል ታካይ ርእስ ባለውና ለምረቃ በበቃው በዚሁ ፊልም ውስጥ ይህንኑ ቃለ መጠይቅ ካካሄዱት ከእነዚህ ግብረ ሰዶማውያን ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው ሕጋዊና መደበኛ ሚስት አግብተው፣ ትዳር መስርተውና ልጆች ወልደው በሽምግልና ዕድሜያቸው ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ አዛውንቶች አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ‹‹አባባ መሽቷል እባክዎን ወደ ቤትዎ ሂዱ›› እያሉ ወጣት ግብረ ሰዶማውያን ይቀልዱባቸዋል፡፡ ይሳለቁባቸዋል፡፡ እነዚህም አዛውንቶች ታዋቂነታቸው በ‹‹ዜጎች›› ዘንድ ብቻ ስለሆነና በአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ዘንድ የሚታወቁት ባለትዳርና የልጆች አባት ስለሆኑ ከማኅበረሰቡ ዘንድ እንዳይገለሉና ተከብረው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡ 

የእምነት ቃላቸውን ከሰጡት ግብረ ሰዶማውያን መካከል በቅጽል ስሙ ‹‹ኤሊያና›› በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ወጣት፣ ግብረ ሰዶም መጀመርያ የተፈፀመበት በሐዋሳ ከተማ የሰባት ዓመት ሕፃን ሳለ ነበር፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ መኖር ከጀመረ 32 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ እስካሁን ባሳለፈው ሕይወት ውስጥ ለወሬም የማይመች፣ ከባህል ውጭ የሆነ፣ ሕይወትን እስከመጥላት የሚያደርስና አሰቃቂ የሆነ ወሲብ ከተመሳሳይ ጾታ ጋር ሲፈጸም እንደኖረ ነው የተናገረው፡፡ 

ግብረ ሰዶማውያን የሚፈልጉትን ቆንጆ ወንድ አንዲት ሴት ይዛባቸው ከሄደች ወይም ካወጣችው ‹‹ዓይነጥላ›› ወሰደችብን እያሉ እንደሚያማርሩ ያወሳው ኤሊያና፣ በድሬዳዋ፣ በጅቡቲ፣ በየመንና በሳዑዲ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ይህንኑ የግብረሰዶም ሥራ ያከናውን እንደነበርም አልሸሸገም፡፡ ጅቡቲ የገባው ከድሬዳዋ እስከ ደዋሌ ድረስ በባቡር ከዚያም እስከ ጅቡቲ ደረስ በእግሩ ለአምስት ቀን ያህል ከተጓዘ በኋላ ነው፡፡ ከጅቡቲም በአንድ የሞተር ጀልባ ተደብቆ ወደ የመን እንደተሻገረና በመቀጠልም ሳዑዲ እንደገባ አመልክቷል፡፡ 

‹‹በአገር ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የአምስት ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው የግብረ ሰዶማውያን ሠርጎችን አይቻለሁ፡፡ ይህን ዓይነቱንም ሠርግ መንግሥት ወይም ማዘጋጃ ቤትና ባህል አያውቀውም፡፡ እኛው ራሳችን ነን የምንፈጽመው፡፡ ይህም ሆኖ ፍቅርን ስለማናውቅ በጋብቻ ፀንተን አንቆይም፡፡ ጋብቻው ግፋ ቢል የሚቆየው ለሦስት ወራት ያህል ብቻ ነው፤›› ብሏል፡፡ 
ሚስት የሚሆን ወንድ በሠርግ ሥነ ሥርዓቱ ቀን ቅንድቡን ተቀንድቦ፣ ቻፕስቲክ ተቀብቶ፣ ፊቱ ላይ ማድረግ የሚገባውን ሜክአፕ ሁሉ አድርጎ፣ ፀጉሩን ተሠርቶና ቬሎ ለብሶ ይቀርባል፡፡ በሥነ ሥርዓቱም ላይ ኬክ እንደሚዘጋጅ ነው የተናገረው፡፡ 

ሠላሳ ሁለት ዓመታት ያህል በግብረ ሰዶም ሕይወት የቆየ፣ ስምንት ጊዜ ድል ባለ ሠርግ አግብቶ የወንድ ሚስት የነበረና በቅጽል ስሙ ‹‹አጠለል›› እየተባለ የሚጠራው ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ግብረ ሰዶማዊነትን መተዳደሪያው አድርጎ የያዘው ሲሆን፣ ይህንንም የጀመረው የስምንት ዓመት ሕፃን ሳለ ነው፡፡ የሴት ሚስት ላለውና በዚህ ላይ ደግሞ 17 የወንድ ሚስቶች ካሉት ግብረ ሰዶማዊም ጋር ትዳር ለመጀመርያ ጊዜ ‹‹17ኛ የወንድ ሚስት ሆኜ ነው ያገባሁት›› ሲል አጠለል ይናገራል፡፡ 

የግብረ ሰዶማውያን መለያቸው ከአለባበሳቸው እንደሚጀምር ይናገራል፡፡ ሁልጊዜ ቁምጣ ሱሪ እንደሚያደርጉ፣ ጠባብ ስኪኒ እንደሚያዘውትሩ፣ ጠልጠል ያለ ቦዲ ቲ ሸርት በመልበስ እምብርት እያሳዩና ያለ ካልሲ ጫማ እያደረጉ እንደሚሄዱ፣ ፀጉራቸውን ሊሞዚ መቆረጥ፣ ጆሯቸውን በተለየ ቦታ ላይ በመበሳት ጌጣ ጌጥ ማስገባትና ሎቲ ማንጠልጠል ናቸው፡፡ ከውጭ አገር የሚረዷቸውም ሰዎች አሉ፡፡ በተለይ ዳያስፖራዎች የጠለልን አድራሻ ይዘው ነው የሚመጡት፡፡ ሲጠሩት ይቀበላቸዋል፡፡ በኢንተርኔትም የሚገናኙበት መንገድ አለ፡፡ በዚህም የተነሳ ደንበኞቻቸው ሲመጡ አይቸገሩም፡፡ በሚፈልጉበት ቦታ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ 

‹‹ሪች›› በመባል የምትጠራዋ ሌላው ግብረ ሰዶማዊት (ሌዝቢያን) ወደዚህ ሕይወት ውስጥ የገባችው በጓደኛዋ ግፊት እንደሆነ፣ በዚህም ሕይወት ከገባች ስምንት ዓመት እንደሆናትና መተዳደሪያዋም ይኸው እንደሆነ ገልጻለች፡፡ ሁለት ቋሚ የሴት ደንበኞችም እንዳሏት ተናግራለች፡፡ አንደኛዋ ደንበኛዋ አዲስ አበባ ውስጥ ኦሎምፒያ አካባቢ፣ ሁለተኛዋ ደንበኛዋ ደግሞ በሐዋሳ ከተማ ይኖራሉ፡፡ በጠሩዋት ቁጥር ትሄድላቸዋለች፡፡፡ ጠሪዎቿም በጣም ሀብታሞች እንደሆኑ ነው የተናገረችው፡፡ በዚህም እርካታ እንደምታገኝ፡፡ ከተመሳሳይ ጾታዋ ጋር ካልሆነ በስተቀር ለወንድ ወይም ለተቃራኒ ጾታ ፍላጎት እንደሌላት አስረድታለች፡፡ 

ብሩክቱ ሌላዋ ግብረ ሰዶማዊት ናት፡፡ ሪታ የምትባል ክልስ የልጅነትና አብሮ አደግ የሆነች ጓደኛ ነበረቻት፡፡ በልጅነታቸው ትምህርት ቤት ሲገናኙና ከትምህርት መልስ ወደየቤታቸው ለመሄድ ሲለያዩ ይሳሳማሉ፡፡ ይህን ዓይነት ሁኔታ ቢያዘወትሩም የልጅነት ነገር እንጂ ወደ ሌላ ስሜት አይመራቸውም ነበር፡፡ ከዓመት ዓመት እያደጉና ነፍስ እያወቁ ሲመጡ በመካከሉ ሪታ ወደ ኢጣሊያ አቀናች፡፡ 

ሪታ ከሄደችበት ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ ግን ተለውጣ መጣች፡፡ የመሳሳማቸው ሁኔታ ወደ ልጅነት መንፈስ መሄዱ ቀርቶ ወደ ወሲብ ቀስቃሽነት ተሻገረ፡፡ በዚህም የተነሳ ውለው ሲያድሩ ፍቅር መሠረቱ፤ ‹‹እወዳታለሁ ትወደኛለች፣ ከእሷ ጋር ግንኙነት ሳደርግ ታስደስተኛለች፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ከገባሁ ሰባት ዓመት ሆኖኛል፤›› ብላለች ብሩክቱ፡፡

ሁሉም ወንዶችና ሴቶች ግብረ ሰዶማውያን ኤችአይቪ ፖዘቲቭ እንደሆኑ፣ በዚህ ላይ ደግሞ የሥነልቡና ችግርና የአአዕምሮ ጭንቀት እንዳጋጠማቸው፣ በተለይም ኤሊያና የኪንታሮት በሽታ እንዳደረበት፣ ሁሉም ከዚህ አስከፊና አስነዋሪ ሕይወት ለመውጣት እንደሚፈልጉ በየተራ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡ 

ሰኔ 23 ቀን 2005 ዓ.ም. በተከናወነው የዶክመንተሪ ፊልሙ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የሁሉም እምነቶች ተከታዮች፣ አባት አርበኞች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ አትሌቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ በዚህም ጊዜ መምህር ደረጀ ነጋሽ (ዘወይንዬ) የማኅበረ ወይንዬ አቡነ ተክለሃይማኖት ሊቀመንበርና የፊልሙ ዋና አዘጋጅ ዓላማውን ሲገልጹ በአገሪቱ እየተከሰተ ያለው ግብረ ሰዶማዊነት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ትውልድንም ምን ያህል እየጎዳ እንዳለ ለማስገንዘብ ነው ብለዋል፡፡

ሦስት ዓመት በፈጀው ጥናታቸው የተገነዘቡት ነገር ቢኖር ከግብረ ሰዶማውያን መካከል አንዳንዶቹ ይህን ድርጊት ሕጋዊ እናደርገዋለን ብለው የሚዝቱና፤ ከፊሎቹ ደግሞ በተቃራኒ ድርጊቱ ለሕይወት ጎጂ በመሆኑ መውጣት አለብን ብለው የወሰኑ መኖራቸውን ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 6/29 ግብረ ሰዶም ወንጀል መሆኑን ይደነግጋል፡፡ አንቀጽ 6/32 ደግሞ በዚህ ተግባር የተገኘ ከቀላል እስከ እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ያስቀጣል ይላል፡፡ መምህር ደረጀ እንደሚሉት፣ የወንጀል ሕጉ ግብረ ሰዶምን ቢከለክልም ግብረ ሰዶማዊነት በአገሪቷ በድብቅ እየተስፋፋ ነው፡፡ ራሳቸውን አጋልጠው የሚወጡ ሰዎች ቢኖሩም ራሳቸውን ባላጋለጡት ተፅዕኖ ያደርስባቸዋል፡፡ 

ዶክመንተሪ ፊልሙ በኢትዮጵያ ግብረ ሰዶማዊነት መኖሩን በግልጽ በሚመሰክሩ ሰዎች አማካይነት ለመንግሥትና ለኅብረተሰቡ ማሳወቅና ከድርጊታቸው ይወጡና ይታቀቡ ዘንድ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ ለማቅረብ ነው፡፡ 

በፊልሙ ወቅታዊ ሞቅታን ፈጥሮ መለያየት እንደማያስፈልግ የሚናገሩት መምህር ደረጀ፣ በሕፃናት ላይ ግብረ ሰዶማዊ ጥቃት የመፈፀም አካሄድ የሚከተሉትን ግብረ ሰዶማውያን ከወዲሁ ለማቆም በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በሥነ ምግባር ማኅበር ተደራጅቶ በቀጣይነት መሥራት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ 

በግብረ ሰዶም ሕይወት ለብዙ ዓመታት ማሳለፋቸውን በመጥቀስ የሕይወታቸውን እውነታ ለገለጹት የቀድሞ ግብረ ሰዶማውያን ከችግር የተነሳ መልሰው እንዳይገቡበት ኅብረተሰቡና መንግሥት ሊረዷቸው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ግብረ ሰዶማዊነት እየተስፋፋና ግብረ ሰዶማዊ ጥቃትም እየተፈጸመ ስለሆነ ድርጊቱ ከመስፋፋቱና ‹‹ለኛም መብት ይሰጠን›› የሚል ጥያቄ ከመነሳቱ በፊት መንግሥት ከእንጭጩ ሊገታው ይገባልም ብለዋል፡፡ 

የምረቃውም ታዳሚዎች ይህ ዓይነቱን እኩይና ትውልድ ገዳይ የሆነውን ድርጊት ለመግታት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የተናገሩ ሲሆን፤ ከታዳሚዎቹም መካከል አርቲስት ተስፋዬ አበበ ግብረ ሰዶማዊነትን ለመግታት የሚያስችል በአዲስ አበባ ደረጃ አንድ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጠይቀው፣ ለኮሚቴውም ሥራ ስኬታማነት ቀስቃሽና ትምህርት አዘል መልዕክት ያላቸውን ልዩ ልዩ መዝሙሮች ለማዘጋጀት ቃል ገብተዋል፡፡  

Soures Reporter News Paper 

No comments:

Post a Comment