Tuesday 21 April 2015

ሰማዕታተ ሊቢያና የሲኖዶሱ መግለጫ

የቅዱስ ሲኖዶሱን መግለጫ አየሁት፡፡ መጀመሪያ ነገር ቋሚ ሲኖዶሱ ተሰብስቦ መክሮበታል ብዬ ለማመን ይቸግረኛል፡፡ የተጻፈበት ቋንቋ ቤተ ክህነት ቤተ ክህነት አይልም፡፡ ለመሆኑ ለሰማዕታት የሚሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አጥታችሁ ነው? ይበልጥ ያስገረመኝ ደግሞ የሰማዕታቱ ዜግነት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ምን እንደሚጠቅማት ነው፡፡ መንግሥት የዜግነትን ጉዳይ ቢያነሣ ኃላፊነቱ በዜጎቹ ላይ የተወሰነ ስለሆነ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ‹መልዕልተ ኩሉ› የተባለቺውን ዘንግታው ነው የዜግነት ጉዳይ ያሳሰባት? ምንም ኢትዮጵያዊነታቸው የማያጠራጥር ቢሆንም፣ ጠላታቸው እንኳን የመሰከረላቸው ቢሆንም፣ ዓለም ያወቃቸው ቢሆንም፣ ለቤተ ክርስቲያን ግን ሱዳኖችም ሆኑ ሩዋንዳዎች፣ ሶማልያዎችም ሆኑ ጅቡቲዎች የተሠውትኮ ክርስቲያኖች ናችሁ ተብለው ነው፡፡ ለአንድ ክርስቲያን የሰማዕትነት ክብሩ የሞተለት ክርስቲያናዊ ምክንያት ነው፡፡ የሞቱት ደግሞ ክርስቲያኖች ናችሁ ተብለው ነው፡፡ በቃ፡፡ 


ደግሞስ ‹የዜግነትና የማንነት መረጃውን በተመለከተ ግልጽ መረጃ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው› የሚሉን ማነው ጥረት እያደረገ ያለው? መንግሥት ነው ካላችሁ ‹መንግሥት ጥረት እያደረገ ነው› በሉ እናንተም ጥረት እያደረጋችሁ ከሆነ ንገሩን፡፡ ቤተሰቦቻቸውኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ናቸው፡፡ ለምን ለየሀገረ ስብከቱ መመሪያ በመስጠት ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ከበዳችሁ? እረኛ በጎቹን በሪሞት ይጠብቃል እንዴ?

እጅግ ያስገረመኝና ያሳዘነኝ ነገር ደግሞ ክርስቲያን በመሆናቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ለተገደሉ ወንድሞች ከቤተ ክርስቲያን የምጠብቀውን ሦስት ነገር ከመግለጫው ማጣቴ ነው፡፡ የመጀመሪያው የመታሰቢያ ጸሎት ሊደረግ ይገባው ነበር፡፡ በምንም ለማናውቃቸውና ለማያውቁን የኢንዶኔዥያ ዜጎች ሱናሚ መታቸው ብለን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት ያደረግን ሰዎች ለሚያውቁንና ለምናውቃቸው ክርስቲያን ወገኖች ጸሎት ለማድረግ ለምን እንደከበደን እንጃ፡፡ ለመሆኑ ከአንድ አባት ከጸሎት በላይ ምን ሊገኝ ይገባ ነበር?

‹ማንነታቸው ተረድተን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት አስፈላጊውን እናድርጋለን› ይላል መግለጫው፡፡ ለመሆኑ ከክርስትና በላይ ምን ማንነት አለ? የብሔር፣ የብሔረሰብ ማንነት ነው የምታጣሩት? ከዚያ ይልቅ ሁኔታውን የሚከታተል፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኝና ለቀጣዩ የቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊም ቀኖናዊም ተግባር ነገሮችን የሚያመቻች ሲኖዶሳዊ ኮሚቴ ይቋቋማል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ምነው በአንድ አጥቢያ ገንዘብ ተወሰደ ሲባል ሲኖዶሳዊ ኮሚቴ ይቋቋም የለምን?

ሦስተኛው ያሳዘነኝ ነገር ቤተ ክርስቲያን በልጆቿ ላይ የሚደርሰውን ኀዘን የምትገልጥበት ቀኖናዊና ትውፊታዊ ሥነ ሥርዓት የሌላት ይመስል ኀዘንን በሴኩላር መንገድ ስትገልጥ ማየቴ ነው፡፡ እኔ የጠበቅኩት ለአንዳንድ ክርስቲያን ላልሆኑ ‹ታላላቅ ሰዎች› ቀብር እንኳን የሚከፈተው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተከፍቶ፣ ለቢዮንሴ እንኳን ያልተነፈጋት ማኅሌት ተቁሞ፣ በፓትርያርኩ የሚመራ ጳጳሳቱ የሚገኙበት የጸሎት ሥነ ሥርዓት ተደርጎ፣ መግለጫው በጸሎቱ ፍጻሜ ይሰጣል ብዬ ነበር፡፡ የመግለጫው አሰጣጥ ግን የዕለት ተዕለት ተግባርን በተመለከተ የሚሰጥ ሳምንታዊ መግለጫ ነበር የሚመስለው፡፡ ኦርቶዶክስ ኦርቶዶክስ አይሸትም፡፡ የተወካዮች  ምክር ቤት እንኳን የሦስት ቀን ብሔራዊ ኀዘን ሊያውጅ መሆኑን ሲገልጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን የጸሎት ሳምንት አለማወጇ የታሪክ ትዝብት ውስጥ የሚከታት ነው፡፡

እኔ የሲኖዶሱ መግለጫና አገላለጡ ወርዶብኛል፡፡ ሲኖዶሳዊም መስሎ አልታየኝም፡፡ ሊቃውንቱ ያዩት፣ ጳጳሳቱ የተወያዩበት፣ ቅዱሳት መጻሕፍቱ ያሹት፣ ቀኖናዎቹ የዳሰሱት፣ ትውፊቱ የነካው፣ ባሕሉ ያጠነው አልመስልህ አለኝ፡፡ ‹ወይ እንደ እስክንድ ተዋጋ ወይ የእስክንድርን ስም መልስ› አለ ታላቁ እስክንድር፡፡
Daniel kibret

No comments:

Post a Comment