Wednesday 28 September 2016

የተካደ ትውልድ (በ.ሥ)


የተካደ ትውልድ
አይዞህ ባይ የሌለው
ታዳጊ የሌለው
ወይ ጠባቂ መላክ፤ ወይ አበጀ በለው
ደርሶ ከቀንበሩ የማይገላግለው
የተካደ ትውልድ ፤
አብዝቶ የጾመ፤ ተግቶ የጸለየ
ጥቂት መና ሳይሆን፤ ጥይት ሲዘንብ ያየ
እድሜ ይፍታህ ተብሎ ፤ የተወለደ’ ለት
አምባሩ ካቴና፤ ማተቡ ሠንሠለት፡፡
ምቾትን የማያውቅ ፤ ረፍት የተቀማ
አልጋው ያጋም እሾህ፤ ምኝታው የሣማ
የተካደ ትውልድ፤
ሞቶ እንኳ ሬሳው፤ አይላላለት ቀንበር
በዘብ እጅ ተገድሎ፤ በሹም የሚቀበር
ከጡት አስጥል በላይ፤ ኑሮ የመረረው
እንዳይሄድ፤ ጎዳናው፤ የተደናገረው
ድል ያልሰመረለት ትግል ሳይቸግረው
የተካደ ትውልድ
በሥጋ በነፍሱ
በቀልቡ በገላው
ኧረ ምንድን ይሆን ፤ ምንድን ይሆን መላው?

No comments:

Post a Comment