Wednesday 6 March 2013

የወይዘሪት እስራኤል 2013 አሸናፊዋ ኢትዮ እስራኤላዊት


ወጣቷ ወደእስራኤል ያቀናችው በ12 ዓመቷ ነው፡፡ የወይዘሪት እስራኤል የቁንጅናን ውድድር ስታሸንፍ በአገሪቱ ከሚኖሩት ከ100 ሺሕ በላይ ከሆኑት ቤተ እስራኤላውያኑ መካከል የመጀመሪያዋ ለመሆን በቅታለች፡፡ ሃይፋ በተሰኘው ዓለም አቀፍ የስብስባ ማዕከል ውስጥ እስራኤላውያት ቆነጃጅትን አሳትፎ አሸናፊነቱን ቤተ እስራኤሏ ቆንጆ ያቀዳጀበት የመጀመሪያው ውድድር መሆኑን የተለያዩ የእስራኤል ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ 

ይታይሽ የሞዴልነት ልምድ ያልነበራት ቢሆንም በዘርፉ በመሳተፉ ለጥቁር ሞዴሎች ያለውን ዝቅተኛ አመለካከት ለመቀየር እድሉን እንደምትጠቀምበት ተናግራለች፡፡ ይህች ወጣት የእስራኤል ቆንጆዎች ቆንጆ ተብላ ብትሰየምም ለድሏ በሩን የከፈተችላትና ወደ ውድድሩ እንድትገባ ገፋፍታ መንገዱን ያሳያቻት ኖሃ የተሰኘችው ጓደኛዋ እንደሆነች ትናገራለች፡፡ 

ወጣቷ ቆንጆ የእስራኤል ቴሌቪዥን የፕሮግራም አስተዋዋቂ መሆን እንደምትፈልግና እንደ አሜሪካዊቷ ዕውቅ ሞዴልና የታይራ ባንክስ የቴሌቪዢን ትርኢት አቅራቢ እንደሆነችው ታይራ ባንክስ መሥራት እንደምትፈልግ ምኞቷን ተናግራለች፡፡ 

በውድድሩ ወቅት ዳኞቹ ለቆነጃጅቱ በርካታ ጥያቄዎችን ይሰነዝሩ ነበር፡፡ ይታይሽ ከጥያቄዎቹ  መካከል ለአንዱ ምላሽ ስትሰጥ፣ ‹‹እስራኤል በርካታ ጎሳዎችና የተለያየ ቀለም ያላቸው ዜጎች አገር ናት፡፡ በመሆኑም ቤተ እስራኤላውያንን የምትወክል ቆንጆ አሊያም የውበት ንግሥት ለእስራኤል ታስፈልጋታለች፡፡  ይህንን ደግሞ ለዓለም ማሳየት እጅግ አስፈላጊ ነው፤›› ብላለች፡፡ 

ውቧ ይታይሽ የቁንጅና ውድድሩን እንድታሸንፍ በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩ ቤተ እስራኤላውያንና ሌሎች እስራኤላውያን የወጣቷ አሸናፊነት ሲገለጽ በደስታ ሲፈነጥዙ ውድድሩ ከተካሄደበት አዳራሽ ውስጥ በተቀረጹ ምስሎች ታይተዋል፡፡ 

ወጣቷ ማንኛውም እስራኤላዊ አገራዊ ግዴታውን የሚወጣበትን የውትድርና አገልግሎት ከዚህ ቀደም የሰጠች ሲሆን፣ የትምህርት ገበታዋን የተቋደሰችው በአገሪቷ ካሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ኢትዮጵያውያን ብቻ የሚማሩበት ትምህርት ቤት በመሄድ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ማንኛውም እስራኤላዊ በሚማርበት በእስራኤል መንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ ከዜጎቹ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ከመለማመድ አንሥቶ ከትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ጋር በተለያየ መልኩ ተግባብቶ በመማማር ሒደቱ የተሻለች እንድትሆን እንደረዳት ተናግራለች፡፡ 

ዓለም ላይ ካሉ ጀግኖች መካከል ተፅዕኖ ያሳደረባት የትኛው እንደሆነ ስትጠየቅ ‹‹ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው›› ያለችው ይህች ወጣት፣ ለእሷ ምሳሌ የሆነው ማርቲን ለፍትሕና እኩልነት በመዋጋቱ ልትመርጠው እንደቻለች ተናግራለች፡፡ አያይዛም፣ ‹‹እኔም እዚህ ለመገኘቴ አንዱ ምክንያት ይሄ ነው፡፡ በሚዲያዎች ባይነገርልንም በእኛ ቤተ እስራኤላውያን መካከል ያልተነገሩ በርካታ ሰናይ ማንነቶችም አሉ፤›› ያለችው ይታይሽ፣ ውድድሩን ማሸነፏ ተልዕኮ ሆኖላት፣ እስራኤል ጥቁር ዜጎች እንዳሏት ማሳየትና ብዙ ቤተ እስራኤላዊ ሞዴሎች ባለመኖራቸው እሷ ስኬታማ በሆነችበት መንገድ ለቤተ እስራኤላውያኑ ወጣት ሞዴሎች መንገድ የሚከፍትላቸው መሆኑን ተናግራለች፡፡ 

በእስራኤል ቴሌቪዢን የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት የቴሌቪዥን ፕሮግራም አስተዋዋቂ መሆን ሕልሟ የሆነው ይህች ወጣት፣ ወይዘሪት እስራኤል መባሏ በእስራኤል ያሉትን ቤተ እስራኤላውያንን ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቷ የሚገኙትን እስራኤላውያንን መወከል እንዲያስችላትም ተመኝታለች፡፡ 

የዚህች ወጣት የውበት ንግሥት መባል ከኢትዮጵያ የሚሰደዱትን ቤተ እስራኤላውያን በእስራኤል ሲኖሩ የሚያጋጥማቸውን ውስብስብ ሁኔታ፣ መገለልና እንግልትን ለመቀነስ አሊያም ለማስወገድ መልካም አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችልም ተነግሯል፡፡ እስራኤልን ወክላ በዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር ላይ መሳተፍ መቻሏ ለእርሷም ሆነ ለዜጎቿ ታላቅ ክብር መሆኑንም ገልጻለች፡፡
(ቅንብር በምዕራፍ ብርሃኔ)  

No comments:

Post a Comment