Wednesday 4 April 2018

የዐቢይ ንግግር ሰባት አዕማድ



የሀገሬ ሰው ‹ካልተናገረ አይታይ ብልሃቱ፣ ካልታረደ ዓይታይ ስባቱ› ይላል፡፡ ንግግር የሰው ልጅ ከተሰጡት የላቁ ጸጋዎች አንዱ ነው፡፡ ንግግር ሰዎችን ሊያግባባቸው፣ ወደ አንድነትና ኅብረት ሊያመጣቸው፣ ሊያከራክራቸውና ሊያወያያቸው ኃይል አለው፡፡ ከመሪዎች ከሚጠበቁ ነገሮች አንዱ ኃይል ያለው ንግግር ነው፡፡ ኃይል ያለው ንግግር በሚመርጣቸው ቃላት፣ በሚጠቀምበት ድምፀት፣ በሚያቀርባቸው አገላለጦች፣ በሚሰጣቸው ምሳሌዎች፣ በሚቀርብበት ተፋሰስ፣ በሚዋቀርበት አሰካክና በምጣኔው ይታወቃል፡፡ ሊደመጥ፣ ሊነበብ የሚችል፣ በሐሳቡ ባንስማማም በአቀራረቡ የሚማርከን፣ በዝርዝሩ ባንግባባም ሐሳቡ ግን የሚገባን፤ ባንወደውም የምናደንቀው ንግግር ከመሪዎች ይጠበቃል፡፡ ዐፄ ምኒልክ ለዐድዋ ጦርነት ሕዝቡን ለመጥራት ያወጁት ዐዋጅ ከዐዋጅነቱ ይልቅ የመሪ ጥሪ የሆነ ቃል አለው፡፡ በውስጡ ንጉሡንና ሕዝቡን የሚያቀራርብ፣ የሀገሪቱን ችግር የሚገልጥ፣ ከሕዝቡ የሚፈልጉትን የሚያሳይ፣ ሀገር ስትጠራው እምቢ ብሎ የቀረ የሚገጥመውን ዕጣ ፈንታ የሚያመላክት ቃል ነው፡፡ መላዋን ኢትዮጵያ ለአንድ ዓላማ ያሰለፈና ውጤቱን በዐድዋ ተራሮች ላይ ያሳየ ቃል ነው፡፡

በተለይ ደግሞ ሀገር ምጥ ላይ በምትሆንበት ጊዜ የመሪዎች ንግግር ወይ ፈዋሽ ወይ አባባሽ ይሆናል፡፡ ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል እንዲሉ፡፡ አነጋገሩ የሚያግባባ፣ የሚጠራና የሚያቀራርብ ከሆነ ሕዝብን ለመፍትሔ የማሰለፍ ኃይል ይኖረዋል፡፡ ንግግሩ ብቻ ሳይሆን ንግግሩ የተዋቀረበት መዓዝን የመሪውን ጉዞ ካርታውን እንድናይ ያደርገናል፡፡

የዶክተር ዐቢይ አሕመድ ንግግር በንግግሩ ይዘት፣ ንግግሩ በተቀናበረባቸው ቃላት፣ ቃላቱ በተሰናሠሉበት አወቃቀር፣ ሐሳቡ በተገለጠባቸው ምሳሌዎች፣ ማሳያዎች፣ ጥቅሶች፤ ትኩረትና አጽንዖት በተሰጣቸው የሐሳብ ዘውጎች፣ ብርታቱና ድክመቱ ሊተነተንና የመሪዎች ንግግር ምን መሆን እንዳለበት መማማሪያ ሊሆን ይገባዋል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ ንግግሩ የተዋቀረባቸውን ሰባት አዕማድ ለዛሬ ላንሳ፡፡
የዶክተር ዐቢይ የበዓለ ሲመት ንግግር በሰባት አዕማድ የተዋቀረ ነው፡፡ እነርሱም ክብር፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ አንድነት፣ ይቅርታ፣ ሰውነትና ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያዊነት ናቸው፡፡

1.  ክብር፡- ዶክተር ዐቢይ ንግግራቸውን የጀመሩት ከእርሳቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትንና በፈቃዳቸው ሥልጣን ‹ያሸጋገሩትን› አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በማመስገን ነው፡፡ በዚህ ንግግራቸው ግን ክብርና ምስጋና የሰጡት ለእርሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ሰባት አካላትም ክብርና ምስጋና ተሰጥቷቸዋል፡፡

ሀ. ሽግግሩን እዚህ ደረጃ ለማድረስ ሚና ለተጫወቱ፣
ለ. ኢትዮጵያን ለሚያኮራት ታሪካችን፣
ሐ. ለኢትዮጵያውያን የማይበጠስ አንድነት፣
መ. ለኢትዮጵያ ታላቅነት በየዘመናቱ መሥዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን፣
ሠ. በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣
ረ. ለተፎካካሪ ፓርቲዎች፣
ሰ. አሁን ለመጣው ለውጥ ዋጋ ለከፈሉ ኢትዮጵያውያን ተገቢውን ክብር በንግግራቸው ውስጥ  ሰጥተዋቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከታሪክ መዝገብ የተፋቀ ይመስል ከመንግሥታዊ ዲስኩሮች ስሙ ጠፍቶ ለኖረው የካራማራ ድል ተገቢውን ክብር ሰጥተውታል፡፡

ኢትዮጵያውያንን የገለጡበት መንገድም ለዜጎች ያላቸውን ክብር የሚያሳይ ነበር ‹ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት። ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሰርክ የሚተጉልጆችን አፍርታለች። ልጆቿም ወደቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምናፍትህ እንዲጠበቅ፣ ብልጽግና ያለ አድልኦ ለመላው ዜጎች ይደርስ ዘንድአጥብቀው ይመኛሉ… ይደክማሉ። በሀገር ውስጥና በውጪ ሆነው ስለ ሀገርአንድነትና ሰላም… ስለፍትህና እኩልነትእንዲሁም ስለብልጽግና ይጮሃሉይሞግታሉ… ይሟገታሉ።› ነው ያሏቸው፡፡ የዜጎቻቸውን ትግልና ጥረት ክብር ሰጥተውታል፡፡ አሸባሪዎች፣ ነውጠኞች፣ አደገኛ ቦዘኔዎች፣ አላሏቸውም፡፡ ዶክተር ዐቢይ ኢትዮጵያውያን ላደረጉት የዴሞክራሲ፤ የፍትሕ፤ የእኩል ተጠቃሚነት፤ በነጻ ተዘዋውሮ የመኖርና የመሥራት፤ የሕግ አስከባሪ ተቋማት ገለልተኝነት፤ ሕዝብ አገልጋዩን የመተቸት፤ የመምረጥ፣ የመጠየቅ ሙሉ መብትጥያቄና ትግል ክብርና ዕውቅና ሰጥተውታል፡፡ 
 
2. ፍቅር፡- አንድነታችን ፈተና ገጥሞታል፤ ፍቅራችንን የሚያቀዘቅዙ ነገሮች እየተከሠቱ ነው፣ መጠላላቱና መከፋፋቱ በየአቅጣጫው ዕየታየ ነው በምንልበት ወቅት ፍቅርን የሚሰብክ የመሪ መልእክት ኃይል አለው፡፡ የዶክትር ዐቢይ ንግግር ይህንን የተረዳና ማሻሪያ ለመስጠት የተዘጋጀ ነበር፡፡ በሕዝቡ መካከል ከፍቅር ይልቅ ቅሬታ፣ ከወዳጅነት ይልቅ ጠላትነት፣ የሚያጭሩ ቃላትን ላለመጠቀም ጥንቃቄ አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ከደርግ ዘመን ፓርላማ ወዲህ ‹ፀር› ከፓርላማ የተባረረበት የመሪ ንግግር ነበር፡፡ ፀረ አብዮት፣ ፀረ ሕዝብ፣ ጸረ ልማት፣ ፀረ ዴሞክራሲ፣ ፀረ … የሚለውን እንደ ሃሌሉያ አዘውትሮ ሲሰማ ዐርባ ዓመት ላለፈው ፓርላማ እንግዳ ነገር ነው፡፡ ጠባብነት፣ ነፍጠኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሽብርተኝነት፣ የመሳሰሉት የሰለቹ ቃላት ባመሳተፋቸው አዝነው የዋሉበት ንግግር ነበረ፡፡

የዶክተር ዐቢይ ንግግር በ8 ገጽ፣ በ2776 ቃላት፣ በ12533 ምዕራፍ አልባ ቅንጣቶች(Characters without space)፣ በ15230 ባለ ምዕራፍ ቅንጣቶች(Characters with space)፣ በ79 ዐንቀጾችና በ259 መሥመሮች የተዋቀረ ነው፡፡ በዚህ ንግግር ውስጥ በዋናነት የተንጸባረቀው መግለጫ ‹እኛ› የሚለው ራስን ከሕዝብ ጋር የሚያስተሣሥርና ፍቅርን ሊገልጥ የሚችለው አንጓ ነው፡፡ ይህን ለመግለጥ በቃላት ላይ - ችን የሚል ድኅረ ቅጥያ ተጠቅመዋል፡፡ ኢትዮጵያችን፣ ሕዝባችን፣ ሀገራችን፣ ወገናችን፣ ችግሮቻችን፣ ስኬቶቻችን የሚሉ መግለጫዎች አሉ፡፡ በጽሑፉ ውስጥ ይህንን መንገድ ከ86 ጊዜ በላይ ተጠቅመውበታል፡፡ ከዚህ መካከል ከ18 ጊዜ በላይ ‹ሀገራችን› የሚለው መግለጫ ይገኝበታል፡፡

3. አንድነት፡- የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፣ ከማራራቅ ይልቅ የሚያቀራርብ፣ ከመገፋፋት ይልቅ የሚያስተሣሥር፣ ከማግለል ይልቅ የሚያካትት፣ ከመነጣጠል ይልቅ የሚያስተባብር ነበር፡፡ ራሳቸውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ነው ያቀረቡት፡፡ ከመነሻቸው ይልቅ መድረሻቸው ላይ ነው ያተኮሩት፡፡ ራስ ካሣ እንዳሉት ‹ፀሐይን ለብቻዬ ልሙቅ አይባልም›፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የአንድ ወገን አይደሉም፡፡ የጥንቶቹም የዛሬዎቹም፣ የደጋፊዎቹም የተፎካካሪዎቹም፣ የክርስቲያኖቹም፣ የሙስሊሞቹም፣ የሌሎቹም፤ የመረጧቸውም ያልመረጧቸውም፣ የሀገር ቤት ነዋሪዎቹም የዳያስጶራዎቹም ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን አሳይተውበታል፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የትናንቱም የዛሬውም፣ የነገውም ጠቅላይ ሚኒስትር ነውና የቀደሙትን ከዛሬዎቹ ጋር አስተሣሥረው ጠርተዋቸዋል፡፡ በታሪካችን ውስጥ ማሳያ የሚሆኑትን ኩነቶች አንሥተው የእገሌ ጎሳ መሬት ነው ሳይሉ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው በየዘመናቱ የከፈሉትን መሥዋዕትነትና በመሥዋዕትነት ቦታቸው የዚያው ቦታ አፈር ሆነው መቅረታቸውን ገልጠዋል፡፡ ‹በአንድ ሀገር ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሀሳብ ልዩነት እርግማንአይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርሕ ላይ ተመስርተንመግባባት ስንችል የሀሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። በሀሳብ ፍጭትውስጥ መፍትሄ ይገኛል። በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ። ስንደመርእንጠነክራለን። አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም… አገር ይገነባል። የኔሀሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን እንኳን አገርን ሊያቆም ቤተሰብንያፈርሳል። ያለችን ኢትዮጵያ ነች ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ሀገራዊአንድነት ይበልጣል። አንድነት ማለት ግን አንድ ዓይነትነት ማለት እንዳልሆነሊሰመርበት ይገባል። አንድነታችን ልዩነቶቻችንን ያቀፈ ብዝኃነታችንን በኅብረብሔራዊነት ያደመቀ መሆን አለበት።› የሚለው መዓዝናዊ የአንድነት መግለጫቸው ነው፡፡

ይህ ለውጥ እንዲመጣ በየመሥመራቸው የታገሉትን የጠሩበት መንገድ፣ ተቃዋሚ ፓርቲ እየተባሉ ሲጠሩ የኖሩትን ኃይሎች ‹ተፎካካሪ ፓርቲዎች› ብለው የገለጡበት አካሄድ፡፡ ዳያስጶራውን ማኅበረሰብ ያቀረቡበት መንገድ የንግግሩ አንኳር ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ በተለያየ ጊዜ፣መስዋእትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎችና ፖለቲከኞች፤ በቅጡ ሳይቦርቁሕይወታቸውን ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፤ ለሥነ ልቦናዊና አካላዊ ቀውስየተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች› እና ‹ሰላም ለማስከበርና ሕገመንግሥታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ ሕይወታቸውን  የፀጥታ ኃይሎች› ጎን ለጎን የተመሰገኑበት መንገድ አስደናቂ ነው፡፡ መንግሥት ለአንጋቹ እንጂ ለሟቹ የማይወግንበትን አካሄድ ያረመም ነው፡፡

4. ይቅርታ፡- የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከተዋቀረባቸው አዕማድ አንዱ ይቅርታ ነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች ገልጠውታል፡፡ በተለይም ስድስቱ ዋና ዋና ዘውጎች ይጠቀሳሉ፡-

፩. ያሳካናቸው በርካታ ድሎች እንዳሉ ሁሉ በፍጥነት መቀረፍ የሚገባቸውበርካታ ጉድለቶች እንዳሉም እናምናለን። ከስህተቶቻችን ተምረን ወደፊትበመራመድ ማተኮር ያለብን ጉዳይ የተሻለች ሀገር ለሁላችንም በመገንባቱ ላይነው።›፣‹የሁሉም ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እናፖለቲካዊ ተሳትፎ ከማሳደግ አንጻር ክፍተቶች ነበሩ።› የሚለው ስሕተትን የሚያምነው፤

. ‹ወቅቱ ከስህተታችን ተምረን አገራችንን የምንክስበት ወቅት ነው!› የሚለው ወቅቱን ከስሕተት አንጻር የገመገመው፡፡

፫.  ‹በተለያየ ጊዜ፣ መስዋእትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎችና ፖለቲከኛች፤በቅጡ ሳይቦርቁ ሕይወታቸውን ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፤ ለሥነ ልቦናዊና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታእጠይቃለሁ› የሚለው ለተፈጠረው ችግር ይፋዊ ይቅርታ የሚጠይቀው፣

.‹በአገር ውስጥም ሆነ በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንናትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውንምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍእንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ› የሚለውና ከሌላውም ወገን ይቅርታን የሚጠይቀው ንግግር ይቅርታውን በየደረጃው የጠየቀ ነው፡፡

.  ‹መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው!› ሲሉም ይሄንኑ አጽንተውታል፡፡ ይህም እንዲሳካ

፮.‹በአገር ውስጥም ሆነ በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንናትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውንምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍእንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡› ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

5. ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፡- ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ናት? እነዚህን 12 መግለጫዎቻቸውን እንመልከት፡-

 ሀ. ኢትዮጵያ ማኅጸነ ለምለም ናት
ለ. ትላንት፣ አባቶቻችን በመተማ፣ በማይጨውና በካራ ማራአጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርናበአንድነት ያቆይዋት አገር አለችን።
ሐ. እኛ ዕድለኞች ነን። ውብ አገር አኩሪ ታሪክ አለን። እኛ መነሻችንንእናውቃለን። በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ዝብ ነን።
.ኅብረታችን ለዓለም ምሳሌ መሆን ይችላል። ጠላቶቻችንንአንበርክኳል። ሉዓላዊነታችንን ጠብቆ ዛሬ ላይ ከማድረሱም በላይለሌሎች ሕዝቦችም የነጻነት ትግል አርአያ ሆኗል።
ሠ. ማንነታችንን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖየተገመደ፣የተዋደደ እና የተዋሐደ ነው!
.የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖርኢትዮጵያ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን።
. ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር፤ የሁላችን ቤት ናት!
ሸ. ያለችን ኢትዮጵያ ነች ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ሀገራዊ አንድነትይበልጣል።
ቀ. እኛ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲና ነጻነት ያስፈልገናል፣ ይገባናልም !በ. ኢትዮጵያ የጋራችን፣ የኛ የሁላችን መሆኗን ተገንዝበን የሁሉምድምጽ የሚሰማበት፣ ሁላችንንም የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትየመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን።
. ኢትዮጵያችን፣ አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን  ቸ. እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሥራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያንተሸክሟት ይዞራል። ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያንከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባልም ለዚህ ነው። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ኢትዮጵያዊነትን ከዜግነት በላይ ሐሳብ፣ ፍልስፍናና ሀገራዊ መርሕ አድርጎ ያቀረበ ነው፡፡
ይህንንም በአንድ አንኳር ‹ኢትዮጵያዊነት ያስተማረን እውነታበጊዜያዊ ችግሮች ተሸንፎ መውደቅን ሳይሆን ፈተናዎችን ወደ ዕድልና መልካምአጋጣሚቀይሮ ድል መቀዳጀትን ነው።› ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ‹ኢትዮጵያዊነት› የሚለውን ሉዓላዊ ሐሳብ በክብር ገልጠውታል፡፡

 6. ሰውነት፡- ማንኛውም መሪ፣ መሪ ከመሆኑ በፊት ሰው ነው፡፡ አብዮታዊ ነን የሚሉ መሪዎች ሰውነትን ይተውትና ተቋማዊነትን ቦታ ይሰጡታል፡፤ ከሰው የተወለዱ፣ ሰው ያሳደጋቸውና የሰው ፍሬዎች መሆናቸው ይረሱታል፡፡ መነሻቸውን ከሰው ሳይሆን ከድርጅት ያደርጉታል፡፡ የዶክተር ዐቢይ ንግግር አንዱ ዓምድ ለሰውነት የሰጠው ቦታ ነው፡፡ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ዳያስጶራዎች፣ መሥዋዕትነት የከፈሉ ዜጎች የተነሡበት መንገድ ለሰውነታቸው ቅርብ በሆኑ ቃላት ነው፡፡ እንደ ቡድን የሚያይ ሳይሆን ለግለሰብነታቸው ዋጋ የሚሰጥ ነው፡፡ ዳያስጶራዎች በምንም ዓይነት የፖለቲካ መሥመር ውስጥ ቢሆኑም ‹ሁላችሁምበታታሪነታችሁ፣ በልቀታችሁ እና የትም በሚከተላችሁ የሀገራችሁ የጨዋነትባሕሪ የኢትዮጵያና የዕሴቶቿ እንደ ራሴዎች ናችሁ።› የሚለው ገለጻ ግን የማይመለከተው የለም፡፡ ‹አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክሀብት ባላቸው ነገር ግን እጅግ በበለጸጉ ሀገራት ውስጥ ራሳችሁን ስታገኙትስለሀገራችሁ ቁጭት ሳይሰማችሁ አይቀርም።› ሲል ቁጭታቸውን ይቆጫል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ‹እንደጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሀሳብ አለኝብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ› ለማየት ጥረዋል፡፡ ከድርጅቶቹ ይልቅ ሰዎቹን ‹ወንድም፣ ዜጋ› እያሉ በሰውነት ጠርተዋቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩም እናታቸውን፣ ባለቤታቸውንና የትግል አጋሮቻቸውን ያመሰገኑበት መንገድ ሰውዬው ሰው ናቸው እንድንል የሚያደርግ ነው፡፡ እናታቸውን ከኢትዮጵያውያን እናቶች አንዷ አድርገው፣ ባለቤታቸውን ሚና ከኢትዮጵያውያን ሚስቶች ጋር አስተሣሥረው የገለጡበት መንገድ ‹ሰውነት› የታየበት ነው፡፡ ሰው ከሆኑ ደግሞ እንደሰው ይሠራሉ፣ እንደሰውም ይሳሳታሉ፡፡

7. ተስፋ፡- ሰባተኛው የንግግሩ ዓምድ ተስፋ ነው፡፡ ምን ሊሠሩ አስበዋል? ምን እንጠብቅ? ሊሠሩ ያሰቡትን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች አካላት የሚፈልጉትንም ገልጠውበታል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ውስጥ ቃል መግባትንና ጥሪን የተመለከቱ 19 ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህም፡-
       i.   ይህ የሥልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ ታሪካዊ እድልነው፤ በመሆኑም በከፍተኛ የኃላፊነት  ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል።

ii.  በሀገራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ ነጻነትና ፍትሕ እንዲሰፍን፣ የሕግየበላይነት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን 
ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉያለውን ክፍተት እንሞላለን።

iii.  ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባትእንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን። 
የበኩላችንንም እንወጣለን።

iv.  ኢትዮጵያችን፣ አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆንለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ 
እንድናደርግ በትህትና እጠይቃችኋለሁ

v.   አሁን በጀመርነው አዲስ ምዕራፍ፣ ዘረፋን፣ የሀብት ብክነትን እናየተደራጀ ሙስናን፣ መላው ሕዝባችንን 
በሚያሳትፍ እርምጃ ለመመከትሌት ተቀን እንተጋለን።

vi.   በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን እና ከቴክኒክ እና ሙያኮሌጆች የሚወጡት ተማሪዎቻችን 
ከሚገበዩት ዕውቀት የሚነጻጸርከሂሎት እንዲኖራቸው ከፍተኛ ጥራት ይደረጋል።

vii.  የሁለተኛውን የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የሁሉት ዓመት ተኩልአፈጻጸም በመገምገም አስፈላጊ 
የሆኑ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን ለማስቀጠል እንታገለን

viii.  ኢትዮጵያ ለወጣቶቿ ተስፋ የምትሰጥ እንጂ፣ ተስፋ የምታስቆርጥ አገርእንዳትሆን የምንችለውን ሁሉ 
እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ።በሚቀጥሉት ጊዜያት ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር ብቻ ሳይሆንወጣት 
ባለሀብቶች በብዛት እንዲፈጠሩ እንሠራለን። ለዚህ እንቅፋትናመሰናክል ለሚሆኑ አመላካከቶችና የተንዛዙ 
አድሏዊ የሆኑ አሠራሮችተወግደው ፍትኃዊ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት እንዲኖረንመንግሥት ምቹ ሁኔ
ይፈጥራል።

ix.   መንግሥታችን ከዚህ ቀደም ከነበረው ፍጥነት እና የትግበራ ስኬት በላቀመልኩ ለሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በቁርጠኝነትይሠራል።

x.   ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር እና ሀብት የማፍራትመብታቸው መከበር አለበት። 
በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ተገቢ ያልሆነድርጊት እንዲያበቃና ዳግም እንዳይፈጠር መሥራት ይኖርብናል።

xi. በቀሪው የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዓመታት ቀሪየልማት መርሐ ግብሮቻችንን በፈጠነ ጊዜ ለማሳካት ጥረት ይደረጋል።

xii.   ከመደበኛው የሥራ ሰዓታችን በሚሻገር ጊዜ፣ ከፍ ባለ ፍጥነትና ተነሳሽነትበመሥራት በቅርብ ዓመታት 
ውስጥ በተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋትየደረሰብንን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት ለማካካስ አገራዊ ንቅናቄ
እንድናደርግ ከአደራ ጭምር መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

xiii.   ዕውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ ሀገራችሁ መመለስናሀገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተንእንቀበላችኋለን።

xiv.   በውጭ ሀገራት ኑሯችሁን ላደረጋችሁትም ቢሆን በማንኛውም መልኩበሀገራችሁ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ
 እንድትሆኑና ሀገራችንን በሙሉምመልክ ለመቀየር ለምታደርጉት አስተዋጽኦ መንግሥት ያልተቆጠበ ድጋፍ 
ማድረጉን ይቀጥላል።

xv.   ከጎናችን የቆማችሁ የልማት አጋሮቻችን የሀገራችን ጥብቅ ወዳጆችእንደሆናችሁ እንገነዘባለን። የሀገራችንን ልማት እና ሰላም ለማረጋገጥበምናደርገው ጥረት እንደ ወትሮ ሁሉ ከጎናችን እንደምትቆሙ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።

xvi.   ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት በማበጀት ሕዝባችንን እንደምንክስም ጭምርበዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ፡፡

xvii.   በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገለግሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ
 የሚጥሉ፤ ብሔራዊጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆአስተዋይነትና ሀገራዊ 
ፍቅር፤ በሰጥቶ መቀበል መርሕ የተሻለ የፖለቲካባህል ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን
አስተላልፋለሁ፡፡

xviii.   ሁላችንም የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት እንረባረብሀገራችንን ከድህነትአዘቅት ውስጥ ለማውጣት እንትጋዘረኝነትና መከፋፈልን ከሀገራችንእናጥፋየተማረና በምክንያት የሚከራከር ዜጋ እንፍጠር!

xix.   ከግድቡ መጠናቀቅ ባሻገር የሀገራችንን ብልጽግና እስከምናረጋግጥበትከፍታ ድረስ እንድንዘልቅ ጥሪዬን 
አቀርባለሁ፡፡

ከእነዚህ መካከል 11ዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወይም መንግሥትን የሚመለከቱ ሲሆኑ 8ቱ ደግሞ ጥሪ  ተደረገላቸውን አካላት የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ይህም የችግሩ ዋና መነሻ የመንግሥት አካሄድ ነውና የመፍትሔው ዋና ቁልፍም በመንግሥት እጅ መሆኑን ያሳያል፡፡

 የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃልና ጥሪ 19 ርእሰ ጉዳዮችን የተመለከተ ነው፡፡

፩. የሥልጣን ሽግግሩን አጠቃቀም
፪. የዴሞክራሲ ጥያቄ
፫. የፍትሕ ጥያቄ
፬. የኤርትራን መንግሥት የተመለከተ
፭. ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት
፮. ሙስና
፯. የትምህርት ጥራት
፰. የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ
፱. የኢኮኖሚ ፖሊሲው ማሻሻያ
፲. ለወጣቱ ምቹ የምትሆን ሀገር
፲፩. የሴቶች ተጠቃሚነት
፲፪. ከቦታ ቦታ የመዘዋወርና የመሥራት መብት
፲፫. በተፈጠረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኪሣራ የተቸገረውን ሕዝብ መካስ
፲፬. የተፈጠረውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኪሣራ የሚያካክስ ሥራ መሥራት
፲፭. ዳያስጶራ
፲፮. የልማት አጋሮች
፲፯. ተፎካካሪ ፓርቲዎች
፲፰. ዘረኝነትና መከፋፈል
፲፱. የሕዳሴው ግድብ ናቸው፡፡

እነዚህን ነገሮች ተግባራዊ አድርጎ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኝነት፣ ቁርጥ ያለ ዕቅድ፣ አካታች የሆነ አካሄድ፣ ሳይዘናጉ መፍጠንና ከአንኳር የሕዝብ አካላት ጋር መወያየትን ይጠይቃል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ተጉዞ የተለየ ውጤት ማምጣት አይቻልም፡፡ ‹ቃል ይቀድሞ ለነገር› ነውና ይህ ቃል የነገው ተግባር መግቢያ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን ታሪክ እንደታየው ሕዝብ ዕድል ይሰጣል፡፡ ሕዝቡ የሰጠውን ዕድል የማይጠቀሙ መሪዎች ሲገጥሙት ግን በአሳቻ ሰዓት እንደተመካከረ ሰው ‹ሆ› ብሎ ይነሣል፡፡ ዝምታውን እንደ መሸነፍና ፍርሃት የሚቆጥሩ መሪዎች ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ የሀገራችን ሊቃውንት ሁለት ዓይነት መብራት አለ ይላሉ፡፡ አንዱ ፏ ብሎ የሚበራና መንገዱን ወገግ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ከሩቁ ሆኖ መድረሻን የሚጠቁም መብራት ነው፡፡ የመጀመሪያው ከተገኘ መንገዱን ያለ ዕንቅፋት ለመሄድ፣ በቶሎም ለመድረስ ይመቻል፡፡ እርሱ ካልተገኘ ደግሞ ማዶ ተሰቅሎ መድረሻውን የሚጠቁመው መብራት መኖር አለበት፡፡ መንገዱን ወገግ አድርጎ ባያሳይም መድረሻውን ያመለክታል፡፡ የሚጓዘው ሰው እየወደቀም እየተነሣም ይሄዳል፤ መድረሻውን ያውቀዋልና፡፡ በሩቁ ስለሚያየው አይስተውም፡፡ ተስፋ አይቆርጥም፣ እንደሚደርስ ርግጠኛ ነውና፡፡ ድቅድቅ ጨለማ ግን እንኳን ለሀገር ለግለሰብም አስቸጋሪ ነው፡፡ የዶክተር ዐቢይ መንግሥት ይህ የሕዝብ ድጋፍና ፍቅር እንደ በረዶ ከመቀዝቀዙ በፊት ቢችል መንገዱን ያብራ፣ ባይችል መድረሻውን ያሳይ፡፡ ካልሆነ ግን ምናልባት ሌሎቹ ቀደምቶቹ ያገኙትን ዕድል ላያገኘው ይችል ይሆናል፡፡ ሰው የሚጠየቀው በተሰጠው መጠን ነውና፡፡ አሁን ተግባሩን እንጠብቃለን፡፡ ችግሮቹን ሁሉ እንዲፈቱ ሳይሆን መፍታት እንዲጀምሩ፤ ስሕተቶቹን ሁሉ እንዲያርሙ ሳይሆን ማረም እንዲጀምሩ፤ መንገዱን በሙሉ እንዲሠሩ ሳይሆን መሥራት እንዲጀምሩ፡፡

ወቅቱ የትንሣኤ ዋዜማ ነውና እባክዎን ሥራዎትን መፈታት የሚገባቸውን የፖለቲካ እሥረኞች (በተለይም ደግሞ ይህንን የእርስዎን ንግግር ከእሥር ቤት ውጭ እንዲሰሙ ከተፈቱ በኋላ፣ እሥር ቤት ተመልሰው የሰሙትን እነ እስክንድር ነጋን) ና መነኮሳቱን በመፍታት ይጀምሩ፡፡ የእርስዎም የሕዝቡም ፋሲካ ደርብ ፋሲካ እንዲሆን፡፡ 
ይቅናዎት፡፡

No comments:

Post a Comment