Wednesday 11 July 2018

ለውጥን ባልተለወጠ ሰው እንደማካሄድ ያለ ከባድ ነገር የለም


ከገበሬዎች ጥበብ አንድ እናንሣ፡፡



ጉንዳን ቤቱን ሲወርረው አንድ ቁራጭ ሥጋ ያመጣሉ፡፡ መሐል ወለሉ ላይ ይጥሉታል፡፡ ዓላማ ሰንቆ በአንድ የጉንዳን ንጉሥ እየተመራ በሰልፍ የገባው የጉንዳን ሠራዊት ነገር ዓለሙን ሁሉ ትቶ እየተተራመሰ ወደ ቁራጩ ሥጋ ይሰበሰባል፡፡ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ሥጋው ላይ ይሠፍራል፡፡ ገበሬዎቹ ሁሉም ጉንዳን አንዱ በሌላው ላይ እየወጣ እስኪቆነስ ድረስ ይጠብቁትና ያንን ሥጋ አውጥተው ይጥሉታል፡፡
ከጉንዳን የተሻለ አእምሮ ሳይዙ ለውጥን ማራመድ በአጭር ለመቀጨት ራስን አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ በዓላማ የታገልንበትን፣ የዘመትንበትንና የተሰለፍንበትን ዋና ነገር ከየአቅጣጫው የሚወረወሩ ቁራጭ ሥጋዎች ሲያስቱን እንደማየት አስቂኝም አሳዛኝም ክስተት የለም፡፡ የሆኑ ብልጦች ቁራጭ ነገር በመንገዳችን መካከል ይወረውሩልናል፡፡ እኛም ጅሎች መንገዳችንን እንተወዉና ወደተወረወረው ቁራጭ ሥጋ እንሯሯጣለን፡፡ እዚያ ላይ እንደ ጉድ እንሠፍራለን፡፡ ያን ጊዜ እኛን ከዓላማችን አውጥቶ መጣል ቀላል ይሆናል፡፡ መቼም ለውጥን ባልተለወጠ ሰው እንደማካሄድ ያለ ከባድ ነገር የለም፡፡ ቁርጥራጭ ሥጋዎችን ትተን ወደ ዓላማችን እንገሥግሥ፡፡ ሪከርድ ለመስበር እየሮጠ፣ መንገድ ላይ ለሚሳደብ ሰው መልስ የሚሰጥ አትሌት የለም፡፡ ወይ ጅል ወይ ቂል ካልሆነ በቀር፡፡



Daniel Kibert

No comments:

Post a Comment