Monday 5 November 2012

አልሠለጥን ያለው የዳያስፖራ ፖለቲካ

ዳዊት (እውነተኛ ስሙ እንዲገለጽ አይፈልግም) በኖርዌይ ለአምስት ዓመታት ያህል ቆይታ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቤተሰቡን እዚያ ትቶ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ሥራዎች የተሰማራ ወጣት ነው፡፡ በተሰማራበት ሥራም ውጤታማ ሳይሆን አይቀርም ደስተኛ ነው፤ ቤተሰቡን ለማምጣት ካልሆነ በስተቀር ተመልሶ እዚያ አገር የመኖር ፍላጎት የለውም፡፡ በኖርዌይ ውስጥ በነበረው ቆይታ ብዙም መልካም ትውስታ ያለው አይመስልም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የግል ባንኮች መካከል ስሙ ከሚጠቀስ አንድ ታዋቂ ባንክ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ በቂ የሚባል ደመወዝ እየተከፈለውና መኪና ተመድቦለት፣ እንዲሁም የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እያገኘ መልካም የሚባል ኑሮ የሚኖር ሰው፣ በሥራ ምክንያት ወደ ኖርዌይ አቅንቶ እዚያው ስለመቅረቱ ዳዊት አውግቶናል፡፡

‹‹ዛሬ ነገ እየተባለ የፖለቲካ ጥገኝነቱ ምላሽ አግኝቶ እዚያው አገር የተሻለ ሥራ ሠርቶ ለመኖር የነበረው ምኞት ሳይሳካ የባንኩ ሰው ይኼው ሁለት ዓመት ሞልቶታል፤›› ይላል ያንን የመቅረት ዕርምጃ የወሰነበትን ቀን እየረገመ እንደሚኖር እያስታወሰ፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውን ምንም የፖለቲካ ዕውቀትና ፍላጎት ሳይኖራቸው እዚያ አገር የመኖርያ ፈቃድ አግኝተው ለመኖርና ሕይወታቸውን ለመቀየር ሲሉ፣ ላቀረቡት የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ ምላሽ ሲጠባበቁ እየተሰቃዩ ይኖራሉ ይላል፡፡


በጣም የሚገርመው በማለት ከዚህ ገጠመኝ በተጨማሪ ሌላ ተመሳሳይ ጨዋታም ቀጥሏል፡፡ ከሁሉም በላይ ዳዊትን ቀልቡን የሳበው ግን አንድ ጉዳይ ነበር፡፡ በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ የታቃውሞ እንቅስቃሴ ለማድረግ በአገሪቱ መንግሥት ድጋፍ የሚሰጡዋቸውን ቤቶች አከራይተው ስለሚኖሩ ሰዎች እንዲህ ይላል፡፡ ከሚያከራዩዋቸው ቤቶች በሚያገኙት ገቢ ብቻ ኑሮአቸውን ይገፋሉ፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሥራ የላቸውም፤ አያፈላልጉም፤ ሥራቸው የኢትዮጵያ መንግሥትን መቃወም ብቻ ነው ይላል፡፡ በየቀኑ ስለ ኢትዮጵያ መንግሥት የራሳቸውን አዳዲስ መረጃዎች ይፈጥራሉ የሚለው ዳዊት፣ ለአገሪቱ መንግሥት ያቀብላሉ፣ በአካባቢው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ይነግራሉ፤ ያስነግራሉ ይላል፡፡ በሳምንት ውስጥ አብዛኛዎቹን ቀናት በብዛት የሚያሳልፉት ቤት ወስጥ ተሰባስበው ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው የገፋ ቢሆንም በየቀኑ የሚያወሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጸሙ ስለሚባሉ ግፎችና የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ነው፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ መረጃ የሚያቀብሉዋቸው ታማኝ ምንጮች እንዳሉዋቸው ያሳምናሉ ሲል ዳዊት ትዝብቱን ይናገራል፡፡

ፖለቲካቸው በአብዛኛው በብሔር ላይ ያጠነጠነ መሆኑን፣ አንዳንዴም በፍብረካ በሚያስወሩት ወሬ ምክንያት እዚው አካባቢ በሥራ ተሰማርተው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካካል የጎሳ ግጭት እንዲነሳ መንስዔ መሆናቸውን ያወሳል፡፡ በማያውቁት ነገር ተጣልተው እስር ቤት የሚገቡ ብዙ መሆናቸውንም ያስረዳል፡፡

ይኼም ብቻ አይደለም፡፡ ከእነሱ ጋር አንድ ብሔርን እየነጠሉ የማይሳደቡ፣ እነሱ የሚሉትን ተቀብለው የማያስተጋቡ፣ ጥያቄ የሚያነሱ፣ መንግሥትን የማይቃወሙ ኢትዮጵያውያንን በመሉ ‹‹በወያኔነት›› ይፈርጃሉ ይላል፡፡ ‹‹ሌቦች፣ ከሃዲዎች፤…›› የሚሉ ታፔላዎች እንደሚለጠፉባቸው ይናገራል፡፡

ዳዊት ስለ አንድ ነገር በግርምት ያወሳል፡፡ አንደኛው መንግሥትን የሚደግፍ ብቻ ሳይሆን፣ የማይቃወም ነገር ግን እነሱ ያወሩትን ያልተቀበለና ያላሰራጨ፣ እነሱ ከሚሉት ውጭ እዚህ አገር ስላለው ሁኔታ ምንም ነገር ያወራ በመሉ ‹‹ወያኔ›› ብለው መፈረጃቸው ነው፡፡ ሁለተኛ ምንም ነገር ውስጥ የሌለበትንና በማናቸውም የሥራ መስክ የተሰማራ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ይጠላሉ፡፡ ከእነሱ ዓላማ በተፃራሪ ወይም መሀል ሰፋሪ የሆኑትን በመሉ በሐሰት በመወንጀል ያስገርፋሉ፣ ያሳስራሉ፣ እንዲባረሩ ያደርጋሉ ይላል፡፡

ሲፈልጉም በሐሰት ምስክር አስመስክረው ያስፈርዳሉ ሲል ዳዊት፣ የአገሩ መንግሥት አያጣራም እንዴ? ማለቴ አልቀረም፡፡ ኖርዌይ ውስጥ በሐሰት ከተመሰከረብህ ፍርድ ቤቱ ይቀበላል ነው የሚለው፡፡ ባህላቸው እንደዚያ ነው በማለት፡፡ ‹‹ሰው የሚዋሽ አይመስላቸውም፡፡ አብዛኛዎቹ ስደተኞች የፖለቲካ ጥገኝት የጠየቁ ሲሆኑ፣ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እስካለ ድረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባት አይፈቀድላቸውም፡፡ በአብዛኛው ተስፋ የቆረጡ ናቸው፡፡ ፀሎታቸው በማናቸውም መንገድ የመንግሥትን ውድቀት ማየት ነው፤›› በማለት አስተያቱን ሰጥቷል፡፡

ዲያስፖራው የፖለቲካ ወይስ የኢኮኖሚ ደስተኛ
አሮን ማቴው ቴራዛዝ የተባሉት “Beyond Regrind Circularity the Emergence of Ethiopian Diaspora” በሚል ‹‹ማይግሬሽን ፖሊሲ ኢንስቲትዩት›› የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም በድረ ገጹ ያስነበበው ጽሑፍ እንደሚያመለክተው፣ በተለያዩ ዓለም በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውን የኢኮኖሚ ወይም የፖለቲካ ስደተኞች ናቸው ብሎ መለየት አይቻልም፡፡ በአጠቃላይ ‹‹የስደት ቀውስ›› የሚለው አገላለጽ ብቻ ብዙዎችን ያስማማል የሚለው ይኸው ጽሑፍ፣ በፖለቲካ ምክንያት ወይም ድህነት ባስከተለው የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት አገር ለቀው የተሰደዱትን መለየት በጣም ከባድ ነው ይላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የቀረቡ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው የአፍሪካ አገሮች ዜጎቻቸው የሚሰደዱት ወደ ቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው አገር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ ለአጭር ጊዜ ኢትዮጵያን የገዛችው ጣልያን ወስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በንፅፅር ያነሰ ቁጥር ያላቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን በብዛት በስደት የሚገኙበት አገር አሜሪካ ሲሆን እስራኤል፣ ሳውዲ ዓረቢያ፣ ካናዳ፣ ስዊድን፣ ጀርመንና ኖርዌይ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አሁን አሁን ግን ወደ ተለያዩ የዓረብ አገሮች የሚሰደዱ ሴት ሠራተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ይታወቃል፡፡

ቴራዛዝ ከላይ በተጠቀሰው ጥንታዊ ጽሑፍ እንዳሰፈሩት፣ የኢትዮጵያውያኑ ስደት በአራት ጊዜያት ተከፋፍሎ የሚታይ ነው፡፡ ይኼም እ.ኤ.ኤ ከ1974 በፊት፣ ከ1974-1982፣ ከ1982-1991 እና ከ1991 በኋላ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን የስደት ዘመን ተጀምሮ መሰደድ የበዛው ደርግ ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስደተኞቹ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከእልቂት ለማትረፍ ያደረጉት ስደት እንደሆነም በስፋት ይወሳል፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 የአሜሪካ የሕዝብ ቆጠራ ውጤት እንደሚያስረዳው ግን 62 በመቶ ወደ አገሪቱ የገቡት ኢትዮጵያውያን በ1990 እና በ2000 መካከል ሲሆን፣ 28 በመቶ የሚሆኑ ደግሞ ብቻ በ1980 እና በ1990 መካከል ደርሰዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 በተደረገው ሌላ ቆጠራ ደግሞ ሁለተኛው ትውልድ ተደርገው የሚቆጠሩት (second generation) 103 ሺሕ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ የተወለዱ ናቸው፤ ይኼ በአገሪቱ ከሚገኙት ትውልደ አፍሪካውያን 12 በመቶውን ይሸፍናል፡፡

የአገር ፀር ወይስ የአገር ተቆርቆሪ?
“The Diaspora politics the case of Ethiopians living in USA” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ የሠሩት አቶ ሳልሃዲን እሸቱ በጥናታቸው ማጠቃለያ አንዳንድ ድምዳሜዎችን ያሰፈሩ ሲሆን፣ በማናቸውም አገራዊ ጉዳዮች ተስማምተው የማያውቁት የሚሉዋቸው መንግሥትና ዋነኛ ተቃዋሚዎች በዳያስፖራው ምንነት ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ይላሉ፡፡ ሁለቱም ወገኖች የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለአገሪቱ ዲሞክራሲ ያደረገው አስተዋጽኦ አሉታዊ መሆኑን፣ ነገር ግን በአግባቡ ቢያዝ ኖሮ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል እጅግ ከፍተኛ ኃይል መሆኑን ጥናቱ ይደመድማል፡፡

ዲሞክራሲ በበለፀገባቸው አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ መቻቻልን የማይፈቅዱ፣ በአገሮቹ ያለውን ጨዋ የፖለቲካ ባህል እንኳ የሚፈታተኑ፣ አክራሪና ጽንፈኛ የፖለቲካ አቋም የሚከተሉ መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በ1960/70ዎቹ በስፋት የታየው የፖለቲካ አካሄድ ኢትዮጵያ ውስጥ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም፣ አሁንም ዲያስፖራው ውስጥ በስፋት ይስተዋላል፡፡ አንዱ የሌላውን የፖለቲካ አቋም አያከብርም፡፡ የራሳቸውን እጅግ የተዘባና የተጋነነ የተሳሳተ መረጃ የሚያዳምጡ እንደሚበዙ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ዓለም የተባሉ ጸሐፊ፣ “Ethiopian extreme Diaspora chicken politics” በሚለው መጣጥፋቸው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ፖለቲከኞች ዓይነትና አመጣጥን መቃኘት አስፈላጊ የሚሆነው፣ በአገር ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚያደርሱ ሆነው ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም ዘንድ የማጉድፍ ችሎታ ስላላቸው ነው ይላሉ፡፡ የቀድሞ ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት (ፖለቲከኞች)፣ የደርግ የቀድሞ ባለሥልጣናት (አባላት)፣ የሥልጣን ጥመኞች (Power mongers group) በሚል ሲከፍሉዋቸው፣ ከመጀመርያውም የሁለተኛውን ቡድን አባላት በዚህ መንግሥት የኢትዮጵያን ውድቀት ብቻ ለማየት የሚከጅሉ ይሉዋቸዋል፡፡

የሥልጣን ጥመኞች ያሏቸው ግን ሥልጣን እስኪይዙ ድረስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ ስለሌለ ‹‹አደገኛ ሰዎች›› በማለት ይጠሯቸዋል፡፡ ምክንያቱም በአገር ውስጥ ምንም ለውጥ ቢመጣም እነሱ ሥልጣን ላይ እስካልወጡ ድረስ አይናቸውን ጨፍነው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው፣ የጥላቻ ፖለቲካ በሽተኞች ናቸው ሲሉ ይሰይሟቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በአጋጣሚ ሥልጣን ላይ የወጡ ጊዜ በጣም ያስፈራል የሚሉት ጸሐፊው፣ ሥልጣን ላይ ለመውጣት ከኤርትራ መንግሥት፣ ከሶማሊያ የአልሸባብ ኃይሎችና ከማናቸውም የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ›› በሚለው መርህ አብረው የሚሠሩ ናቸው ይላሉ፡፡ ኢሳትን፣ የተለያዩ ውጭ ያሉ ድረ ገጾችና ብሎጎችን የእነዚህ ዋነኛ ድምፅ ናቸው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

ዓለም በዚህ ጽሑፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተቃዋሚዎች የሚመች ሁኔታን መፍጠርና በዚያው የአገሪቱን የዲሞክራሲ ምህዋር ማስፋት አስፈላጊነቱ ላይ ቢያተኩሩም፣ በጥላቻ ፖለቲካ የታወሩ ባሉዋቸው በእነዚህ የዳያስፖራ ሰዎች ላይ ግን ይጨክናሉ፡፡ አገር ውስጥ ስላለው የዕለት ተዕለት ለውጥ ለማወቅ የማይፈልጉና የራሳቸውን መረጃ እየፈለጉ የሚያሰራጩ በመሆናቸው ምክንያት ለማግባባት ምን እንደሚደረግ የተጨነቁ ይመስላሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ከጥላቻና ከኃይል ፖለቲካ ወጥታ ወደ ዘመናዊነት እየተሸጋገረች ነች፡፡ እነሱ ግን በጣም ኋላቀር በሆነ መንገድ ላይ በመሆናቸው ምንም አዎንታዊ አስተዋጽኦ አይኖራቸውም፤›› በማለት ይደመድማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የታቃውሞ ፖለቲካ ደካማ መሆኑን፣ ነገር ግን ይህንን ከማጠናከር ውጭ ምንም አማራጭ እንደሌለ ያስገነዝባሉ፡፡

መንግሥትም ተመሳሳይ ድምዳሜ ያለው ይመስላል፡፡ ዳያስፖራን በአገር ልማትና ፖለቲካ ለማሳተፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ፣ በመንግሥት ባለሥልጣናት የተመሩ የልዑካን ስምሪቶች እምብዛም ውጤት የተገኘባቸው አልነበሩም፡፡ መንግሥት የመረጃ ጉድለት ያለባቸውንና መሀል ሰፋሪ የሆኑትን ለማግባባት፣ በአገር ልማት የሚቀኑና የቀድሞ ሥርዓቶች ቅሪቶች ናቸው የሚላቸውን ፖለቲከኞችን ለማግባባት መሞከር ውኃን እንደመውቀጥ ነው ብሎ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ ያሉትም ይኼንኑ ነበር፡፡

የዳያስፖራ ፖለቲከኞች የተቀናጀ የፖለቲካ ዓላማና ፍላጎት የላቸውም የሚሉት አቶ ሳልሃዲን በበኩላቸው፣ ሦስት ስልቶችን መጠቀማቸውን ያስረዳሉ፡፡ አመፅ ማስነሳት፣ ለተቃዋሚዎች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግና የራሳቸውን ሚዲያ ይጠቀማሉ ይላሉ፡፡ አመፅ ለማስነሳት መሞከር እምብዛም ጥቅም አላስገኘላቸውም፡፡ የገንዘብ ድጋፍ አገር ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር የማይጣጣም አጀንዳ ተሸክሞ ስለሚመጣ ብዙም ተቀባይነት የለውም ይላሉ አጥኚው፡፡

አንዳንድ አክራሪ የዳያስፖራ ሰዎችን አገርንና መንግሥትን፣ መንግሥትንና የፖለቲካ ፓርቲን መለየት አቅቷቸዋል ይሉዋቸዋል፡፡ በሚዲያና በሎቢ ሥራ ይኼ ታይቷል ይላሉ፡፡ የበለፀጉ አገሮች ለኢትዮጵያ ዕርዳታ እንዳይሰጡ ይወተውታሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ኢትዮጵያውያን እንዳይጠቀሙ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ለጋሾች የኢትዮጵያን ልማት እንዳይደግፉ የሚቀሰቅሱት በሚዲያዎችና በተለያዩ የቅስቀሳ መንገዶች ነው፡፡ ለተሳሳተ ዓላማ ጥቅም ላይ የዋሉ መሣርያዎች ይሉዋቸዋል፡፡ መንግሥትን በመቃወም ሰበብ የአገር ገጽታን እያበላሹ መሆናቸውን ያሰፈሩት አጥኚው፣ “የቀድሞዋ ኢትዮጵያ” ናፋቂ ቢመስሉም፣ ቀን ተሌሊት የራሳቸው መረጃን በመፈብረክ ጭምር መንግሥትን በሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማጥቃት በሚከተሉት ዘዴ የኢትዮጵያን ስም እያጎደፉ መሆኑን ያምናሉ፡፡

ለዚህ ትልቁን ሚና እየተጫወተ ያለው የመረጃ ክፍተት መሆኑንና መንግሥት አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለማሳወቅ ድክመት አለበት በማለት ችግሩን ያስረዳሉ፡፡ የዳያስፖራው የተጋነነ የሚዲያ የቅስቀሳ ፕሮፓጋንዳ ደግሞ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ሆኗል ይላሉ አጥኚው፡፡

መንግሥትን፣ ተቃዋሚዎችንና የዳያስፖራ ፖለቲከኞችን የሚመለከቱ የመፍትሔ ሐሳቦችን ያቀረቡት አጥኚው፣ መንግሥት በዳያስፖራው ውስጥ የሚታየውን አክራሪነትንና ክፍፍልን በትዕግሥት አይቶ፣ በፖለቲካ ለማሳተፍ አንድ ዕርምጃ መራመድ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ ተቃዋሚዎቹም ከዳያስፖራው ድጋፍ ቢያገኙ እንኳ የራሳቸውን የአገር ውስጥ አጀንዳ ማስቀደም እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፡፡ የዳያስፖራ ሰዎች ከራሳቸው ትዝታና ራሳቸው ከፈጠሩት ብዥታ ወጥተው ያለውን እውነታ ተቀብለው፣ መቃወም ያለባቸውን በሀቅ ላይ በተመሠረተ መረጃ በመቃወም፣ መደገፍ ከፈለጉም እንዲሁ በማድረግ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉና አገርንና ፓርቲን እንዲለዩ ይመክራሉ፡፡

No comments:

Post a Comment