Wednesday 5 June 2013

የግብፅ ፖለቲከኞች የጦርነት ቅስቀሳ በቀጥታ የቴለቪዥን ስርጭት ተጋለጠ





•    ‹‹የመንግሥት ተቃዋሚን በመደገፍ ማተራመስ ወይም ወታደራዊ ጥቃት›› ሲሉ መክረዋል
•    በግብፅ ተቀባይነት ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይቱን አልተቀበሉትም

የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በግብፅና በሱዳን ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ እንዲያጠና በሦስቱ አገሮችና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የተቋቋመው ኮሚቴ በግድቡ ላይ ያቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ከአገሪቱ ፖለቲከኞች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ፖለቲከኞቹ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ካልሆነም በስውር ወታደራዊ ጥቃት ግድቡን ለመምታት መክረዋል፡፡
ነገር ግን ውጥናቸው በስህተት የቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ተጋልጧል፡፡ 

የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ላይ ስለመሆናቸው የማያውቁት በፕሬዚዳንት ሙሐመድ ሙርሲ የተጋበዙት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የልባቸውን ካለመቆጠብ በመናገር፣ እንዴት ኢትዮጵያን ማጥቃትና በግብፅ ብሔራዊ ደህንነት ላይ አደጋ ጋርጧል በሚሉት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ማስተጓጐል እንደሚቻል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ 


በውይይቱ ለተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የእምነት መሪዎች የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ንግግር በማድረግ ውይይቱ ተጀምሯል፡፡ ‹‹አንዲት ጠብታ የዓባይ ውኃ ልንተውላቸው አንፈቅድም፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር አቋማቸውን አስረግጠዋል፡፡ 

ይህንን የፕሬዚዳንቱን ንግግር ተከትሎ መድረኩ ለተሳታፊዎች ክፍት ሲሆን፣ የፖለቲካ አመራሮቹ በጉዳዩ ዙሪያ የግብፅን ጥቅም እንዴት ማስከበር እንደሚቻል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹ግብፅ የኢትዮጵያ መንግሥትን በትጥቅ ትግል እየተቃወሙ ያሉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን መደገፍ ይገባታል፤›› የሚል ሐሳብ ያቀረቡት ዩኒስ ማካዮን የተባሉ የአልትራኮንሰርቫቲቭ ኢዝላሚስት ፓርቲ መሪ ናቸው፡፡ 

‹‹በታጠቁ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች እንቅስቃሴ ምክንያት የአገሪቱ የውስጥ ፖለቲካ በአሁኑ ወቅት በቋፍ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ እነዚህን ኃይሎች በመጠቀም ኢትዮጵያን በማተራመስ ፍላጐታችንን መፈጸም እንችላለን፤›› በማለት ፖለቲከኛው ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ይህም በግብፅ የመንግሥት ቴለቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ሰኞ ዕለት የተላለፈ መሆኑን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡ 

‹‹ይህ ወይም ሌሎች አማራጮች የማይሳኩ ከሆነ ግን ግብፅ የመጨረሻውን ካርታ መምዘዝና መጫወት ግዴታዋ ነው፡፡ ይህም የግብፅን የደኅንነት ተቋም በመጠቀም ግድቡን በወታደራዊ ጥቃት መደምሰስ ነው፤›› በማለት ፖለቲካኛው ተናግረዋል፡፡ አይማን ኑር የተባሉ ሌላ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር በበኩላቸው፣ ግብፅ ለጦርነት እየተዘጋጀች መሆኑን የሚገልጹ ወሬዎችን በመንዛት ኢትዮጵያን ማስጨነቅ ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡ 

‹‹በራሱ ነዳጅ የሚሞላ የጦር ጄት መግዛታችንን የሚገልጽ ወሬ በመንዛት ግድቡን ለመምታት ዝግጅት ላይ እንደሆንን የሚፈጥር ስሜት በኢትዮጵያ ላይ ያነግሳል፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይህ ሐሳብ በኢትዮጵያ ላይ ጭንቀትን በመፍጠር ከእንቅስቃሴዋ ሊገታ የሚችል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጉዳዩ ላይ ኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ውስጥ እንዲከታት ይረዳል በሚል ትንታኔ አጅበውታል፡፡ 

በዚሁ ስብሰባ ላይ የተሳተፉ ሌላ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ግን እንደ ሌሎቹ ስሜታዊነት አልተንፀባረቀባቸውም፡፡ ማዲ ሁሴን የተባሉት እኚህ ግለሰብ በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት መክፈት የሚለውን የሌሎችን ሐሳብ፣ ‹‹አደገኛና የተሳሳተ፣ ውጤቱም ኢትዮጵያን ወደ ጠላትነት መቀየር ነው፤›› ብለውታል፡፡ ባቀረቡት አማራጭ ሐሳብም ቀለል ያለ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ሰላማዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን መክረዋል፡፡ 

በዚህ ውይይት ላይ የተሳተፉት የፓርቲ አመራሮች ያላቸው ተደማጭነት ዝቅተኛ መሆኑን አንዳንድ መረጃዎች የሚገልጹ ሲሆን፣ በዚህ ውይይት ላይ መገኘት ያልመረጡት ፓርቲዎች ጠንካሮቹና በግብፅ ሕዝብ ዘንድም ተቀባይነትን ያተረፉ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በግብፅ ጠንካራ ተቀባይነት ያለው የተቃዋሚ ፓርቲ ጥምረት ናሽናል ሳልቬሽን ፍሮንት የተባለው ፓርቲ አመራር የውይይት ጥሪውን አልተቀበለውም፡፡ 

የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ዳይሬክተር የነበሩት ግብፃዊው ሞሐመድ አልባራዲ የሚመሩት ኮንሲቲቲዩሽን ፓርቲ ፕሬዚዳንቱ ከጠሩት ውይይት ራሱን አግሏል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ በግብፅ መንግሥት ዘንድ ያለው አቋም የጠራና ግልጽ ባለመሆኑ፣ በውይይቱ እንደማይሳተፍ በመግለጽ ራሱን አግሏል፡፡ ይህ ፓርቲ ከውይይቱ በኋላ በሰጠው አስተያየት ውይይቱን ግብፅን ያሳፈረ ብሎታል፡፡ ፍሪ ኢጅብቲያን የተባለው ፓርቲ በተመሳሳይ ከውይይቱ ራሱን ያገለለ ሲሆን፣ የሰጠው ምክንያትም የግብፅ ፕሬዚዳንት ጉዳዩን በተመለከተ ያላቸውን አቋምን በመተቸት ነው፡፡ ‹‹ከውይይቱ የሚፈለገው ውጤት በግልጽ ያልተቀመጠና በጋራ የአገሪቱ ጉዳይ ላይ ድብቅ አጀንዳ የያዘ ነው፤›› በማለት ላለመሳተፍ ወስኗል፡፡ 

ሰኞ ዕለት የተካሄደው ይህ ውይይት በቀጥታ ሥርጭት የተላለፈ ሲሆን፣ የተላለፈው ግን በስህተት መሆኑን የአገሪቱ ባለሥልጣናት እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ትልቅ ስህተት እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ የተሰጠ ምክንያት ግን የለም፡፡ ስህተት መሆኑን ሙሉ ለሙሉ ለመቀበል አዳጋች መሆኑን አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ የሚሰጡት ምክንያትም በቴሌቪዥን ባይተላለፍም የውይይቱ ጭብጥ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ሥጋት ውስጥ መክተት ነው፡፡ በስህተት እንደተላለፈ በመግለጽ የቀረበው የግብፃውያን ሐሳብም ይህንኑ ሥጋት ኢትዮጵያ ላይ ለመፍጠር የሞከረ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡ በአጠቃላይ ይህንን ስህተት በመንግሥት ደረጃ ተሠራ ለማለት ከባድ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ 

ውይይቱ በስህተት በቀጥታ ስርጭት ተላለፈ ከተባለ በኋላ በውይይቱ ላይ የተላለፉ መልዕክቶች የግብፅን አቋም የሚገልጽ አይደለም የሚል የይቅርታ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መንግሥት መላክ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይህ አልሆነም በማለት የውይይቱ በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት መተላለፍ ከጀርባው ምክንያት ሊኖረው ይችላል በማለት አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ 

በእርግጥም በዚህ ጉዳይ ላይ የግብፅ መንግሥት እስካሁን ያወጣው መገለጫ የለም፡፡ ነገር ግን የፕሬዚዳንት ሙርሲ አማካሪ በሰጡት መግለጫ የውይይቱን ተሳታፊዎች ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ውይይቱ በቀጥታ እየተላለፈ መሆኑን ማሳወቅ ይገባን ነበር፤›› በማለት፡፡ 

የቀድሞው የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ዳይሬክተር አልባራዲ በትዊተር ማኅበራዊ ድረ ገጽ በሰጡት አስተያየት ድርጊቱ ግብፅን የሚያሳፍርና ኃላፊነት የጐደለው ነው በማለት በግላቸው የኢትዮጵያና የሱዳን መንግሥታትን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ 

ሴኩላር ሪፎርም ኤንድ ዴቨሎፕመንት የተባለ ፓርቲ አመራር የሆኑት ሙሐመድ አንዋር አል ሳዳት በበኩላቸው፣ ፕሬዚዳንቱ ተወያዮቹን በቅድሚያ በቀጥታ ስርጭት ላይ መሆናቸውን ማሳወቅ ነበረባቸው ሲሉ ተችተዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን በውይይቱ ላይ የተገለጸው ሁሉ የግብፅ መንግሥትን አቋም አይወክልም፡፡ ውይይቱ በኢትዮጵያ ግድብ የተበሳጩ ፖለቲከኞች ወሬ ነው ብሎ መቁጠር ተገቢ ነው፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡ 

ማህመድ ሳላም የተባለ ግብፃዊ የፖለቲካ ተንታኝ በበኩሉ በግብፅ በኩል ኢትዮጵያን በወታደራዊ አቅም አሳንሶ የማየት አባዜን ተችቷል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ነች፡፡ እናም በመሬቷ ላይ ማንኛውንም ግድብ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን አክብራ መገንባት ትችላለች፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ይህንን አልጣሰችም፤›› በማለት አስገራሚ ጽሑፍ አስነብቧል፡፡ 

ከዚህ ይልቅ የኢትዮጵያ ግድብ የሚያደርሰውን ጉዳት በግልጽ መመካከር ተገቢ ነው የሚለው ግብፃዊው ተንታኝ፣ ግብፅ ከምታገኘው የዓባይ ወንዝ ድርሻ ከናስር ሐይቅ ላይ በዓመት 12 በመቶው በትነት ይባክናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የትነት መጠን ከዚህ በግማሽ የሚቀንስ በመሆኑና የግድቡ መገንባትም ውኃውን አመጣጥኖ ለመላክ የሚረዳ በመሆኑ ለግብፅ የሚተነውን በማስረቀት የተሻለ ጥቅም ያስገኛል፡፡ በመሆኑም የግድቡ መገንባት የግብፅ የውኃ ድርሻ ከፍ እንዲል ይረዳል በማለት ይከራከራል፡፡ ኢትዮጵያን ለመውረር ማሰብ ጊዜው ያለፈበት ከንቱ ሐሳብ መሆኑንና ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ መሆኗን ገልጿል፡፡  

‹‹የግብፅ መንግሥት የውኃ ፖሊሲውን በጥልቀት ሊፈትሽ ይገባል፡፡ ከተጋሪ አገሮች ጋርም ያለው ግንኙነት የመተማመንና የመተባበር መንፈስ ጊዜው የሚጠይቀው ነው፤›› ሲል ግብፃውያንን በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰነዝሩ ይጋብዛል፡፡ የግብፅ ባለሥልጣናት የአስዋን ግድብ ግንባታን ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ግድብ ግንባታ በማካፈል ግብፅ የተሻለ ውኃ እንድታገኝ ለኢትዮጵያ እገዛ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲል አስረድቷል፡፡ በዚህ አስተያየቱ ከበርካቶች የአድናቆትና የሙገሳ መልዕክት ደርሶታል፡፡       

No comments:

Post a Comment