Wednesday 30 January 2013

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ጋዜጠኛ ቦፍታ ይማም የዘገባ ልህቀት በማሳየቷ ለኤሚ አዋርድ እጩ ከነበሩ ጋዜጠኞች መካከል ተሸላሚ ሆናለች

ወጣቷ ጋዜጠኛ በምትሠራበት ፎክስ 13 የቴሌቪዥን ጣቢያ ባስመሰከረችው የ‹‹ተከታታይ ዘገባ›› ብቃት እንደሆነ የተለያዩ ድረ ገጾች አስፍረዋል፡፡

ሥራዋን በአሜሪካዊቷ ግዛት በቲኒሲ ከተማ ውስጥ በምትገኘው በሜምፊስ ያደረገችው ቦፍታ፣ ለሽልማቱ የታጨችው በ27ኛው ዙርና ዓመታዊ በሆነው የመካከለኛው ደቡብ ክልል የኤሚ አዋርድ ፕሮግራም ነው፡፡ ሽልማቱ የተዘጋጀው በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጥበብና ሳይንስ አካዴሚ ሲሆን አሸናፊዋ የታጨችበት ምድብ ደግሞ ‹‹ተከታታይ ዘገባ›› ነው፡፡ 

ቦፍታ በዚህኛው ምድብ ብታሸነፍም ከታጨችባቸው ሌሎች ሦስት ምድቦች ውስጥ አንዱ ‹‹የቀላል ፊውቸር›› ዘገባ ነበር፡፡ የወጣቷ ጋዜጠኛ አብዛኛዎቹ ሥራዎቿ ከሚያጠነጥኑባቸው አርዕስተ ጉዳዮች ውስጥ ወንጀልና ፖለቲካ ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ በተጨማሪም በመርማሪ የጋዜጠኝነት ሙያ የምትመሰጠው ቦፍታ፣ ምርጫ ለማሸነፍ በመጓጓቱ ግለሰቦችን ድምፅ እንዲሰጡት በገንዘብ ያማለለ ቺፍ ፖሊስን ማጋለጧ፣ ለሥራዋ ምስክር ከሚሆኑት የምርመራ ዘገባዎቿ ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡

ጋዜጠኛዋ በዘጋቢና በዜና አንባቢነት የምትሠራ ሲሆን፣ በሽልማቱ ምሽት ለምትሠራበት የቴሌቪዢን ጣቢያ ተረኛ ዜና አንባቢ ስለነበረች ሽልማቱን አስመልክቶ የተሠራውን ዘገባ በዜና ሰዓት እንድታነብ ተደርጓል፡፡ 

ቦፍታ የፖሊስና ወንጀል ዘጋቢ በመሆን መረጃዎችን ለተመልካቾች ስታቀብል የቆየች ባለሙያ ነች፡፡ ወጣቷ ጋዜጠኛ ተገቢ ያልሆኑ ፖሊሲዎችን፣ የምትሠራበትን ከተማ ስለሚያስጨንቁት ወሮበሎችና ምስጢራዊ የሆኑ ወንጀሎችንና ያልተገቡ ድርጊቶችን በመመርመር በዘገባዋ ስታጋልጥ ቆይታለች፡፡ በተጨማሪም የልጃገረዶች ሕገ ወጥ ዝውውርን የተመለከተ የምርመራ ዘገባ ማጠናቀሯ ቦፍታ በዋናነት ካጋለጠቻቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ 


ጋዜጠኛዋ ከዘገበቻቸው ጉዳዮች ውስጥ የፖሊሲ ለውጥ የተደረገባቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ በተጨማሪም የቦፍታ ዘገባዎች ላይ ተመርኩዘው ሕግጋት ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ በማስመልከት ብሔራዊ ሥልጠና ከመደረጉም ባሻገር ውሳኔ ሰጪና ሕግ አስፈጻሚ አካላት በወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦችን በቀላሉ እንዲያገኙ የወጣቷ ዘገባዎች ፍንጭ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ 

በጋዜጠኝነት ሙያ ስድስት ዓመታት ገደማ ስታገለግል የቆየችው ቦፍታ ተወልዳ ያደገችው በዋሽንግተን ዲሲ ሲሆን ከሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲም ተመርቃለች፡፡ 

ወጣቷ የተቀበለችው ይህ ሽልማት የመጀመሪያዋ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 ዓ.ም. ‹‹በምርጥ ሰበር ዜናዎች›› ምድብ የኤድዋርድ ሙሮው ክልላዊ ሽልማት አሸናፊ ስትሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2009 ዓ.ም. እና በ2008 ዓ.ም. ደግሞ በኤድዋርድ ሙሮው ክልላዊ ሽልማት ‹‹በወንጀልና ከተማ›› ምድብና በማኅበረሰብ ብሮድካስት ማኅበር በ‹‹ምርጥ የሰበር ዜና›› ምድብ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ 

ቦፍታ መደበኛ ተቀጣሪ ከመሆኗ በፊት በኢንተርንሺፕ ከሠራችባቸው የአሜሪካ ቴሌቪዢን ጣቢያዎች ውስጥ አንዱ ጉድ ሞርኒንግ አሜሪካ ነው፡፡ ጉዞ፣ ሙዚቃ፣ ፊልም፣ የምትኖርበት ሜምፊስ ከተማን መዞር፣ አዳዲስ የምግብ አዘገጃጀቶችን መፍጠርና ከቤተሰብ ወይም ከጓደኞቿ ጋር ጊዜ ማሳለፍን የምትመርጠው ይህች ወጣት፣ በሙያዋ ዋጋዎችን የሚያስከፍሉ ሥራዎችን መሥራቷ ለሽልማት አብቅቷታል፡፡  

No comments:

Post a Comment