Saturday 22 September 2012

”ወንጭፌን አምጡልኝ!”

 የኢሳቱ ደረጄ ሀብተወልድ 

 “ዳዊት ጎልያድን እንዲገጥም ሲላክ የንጉሥ ሳዖልን ካባና ሰይፍ ነበር ያለበሱት።  ሆኖም ልኩ አልሆነም። ካባውም ሰፋው፣ሰይፉም መሬት ለመሬት ተጎተተ። በዚያ መልኩ ወደ ጎልያድ ቢሄድ ኖሮ የሚጠብቀው ዕድል ሽንፈት ነበር። ዳዊት ግን -የንጉሥ ካባና ሰይፍ ስለሆነ ብቻ ፤ልኩ ያልሆነን ትጥቅ ታጥቆ ወደ ፍልሚያው መግባት አልፈለገም። ለዚህም ነው የሳዖልን ካባና ሰይፍ አውልቆ በመጣል ”ወንጭፌን አምጡልኝ!”ያለው። እናም ወንጭፉን አነገተ፤ ጠጠር በኮሮጆው ጨመረ። በግ ጠባቂው ዳዊት ራሱን ሆነ። የሚያውቀውንና የተለማመደውን ወንጭፍና ኮሮጆ አንግቶ ጎልያድን ገጠመ።አሸነፈም።”
 
ደሬ እንዳላቸው አቶ ሃይሌ ከመለስ ካባ እና ሰይፍ ይልቅ የራሳቸውን ወንጭፍ ይዘው ከፊታቸው የሚጠብቋቸውን በርካታ ጎልያዶች ቢሞክሯቸው ይሻላል።
 
አቶ ኃይለማሪያም ከፊት ለፊታቸው ብዙ ጎልያዶች አሉ። እርሳቸው እና ፓርቲያቸው እንደሚለው ድህነት አንዱ ጎልያድ ነው። የፍትህ ማጣት እንዴት ያለ ጎልያድ እንደሆነ ለማወቅ አንድ ጊዜ ቃሊቲ ወይም ቂሊጦ ኧረ ምን ሩቅ አስኬዳቸው እዝችው ማዕከላዊ ሄድ ብለው ማየት ይበቃቸዋል። ዛሬ በሀገራችን የማንበብ እና የመፃፍ ነፃነት በህገ መንግስቱ ላይ ብቻ ነው ያለው። ይሄም ትልቅ ጎልያድ ነው። መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚለው የህገ መንግስት ቃል መከበሩን ለማረጋገጥም ወንጭፋቸውን ማሰናዳት አለባቸው። ሙስናም ቢሆን ዋዛ የሚባል ጎልያድ አይደለም።
 
ዘርዝረን የማንጨርሳቸው በርካታ ጎልያዶች አሉብን እነዚህን ለመፋለም የአቅማቸውን ወንጭፍ ካላዘጋጁ በስተቀር የአቶ መለስን ካባ ለብሰው በአቶ መለስ ሰይፍ ተፋልመው አይችሉትም። ራስዎን መሆን አለብዎ::

No comments:

Post a Comment