Sunday 14 October 2012

ብርሃንና ሰላም የሪፖርተር ጋዜጣን የገጽ ቁጥር ገደበ

በአገሪቱ የሚታተሙትን ጋዜጦች በማተም ከፍተኛውን ድርሻ የያዘውና በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሪፖርተር ጋዜጣን የገጽ ቁጥር ገደበ፡፡ ማተሚያ ድርጅቱ ለጋዜጣው አሳታሚ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽንስ ሴንተር መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በላከው ደብዳቤ፣ የጋዜጣው የእሑድ ዕትም ከ80 ገጽ በላይ እንዳይሆን አስጠንቅቋል፡፡ የማተሚያ ድርጅቱ ይህን የገጽ ገደብ ያስቀመጠው ጋዜጣ ለማተም የሚያገለግለው ወረቀት እጥረት በማጋጠሙ መሆኑን ገልጿል፡፡

በዚህ መሠረት የሪፖርተር የእሑድ ዕትም በአማካይ ከነበረው 150 ገጽ በግማሽ አካባቢ እንዲቀንስ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የጠየቀ ሲሆን፣ በመቀጠልም የጋዜጣው የገጽ ብዛት ከ80 ገጽ እያነሰ ሊሄድ እንደሚችል አሳስቧል፡፡

በአገሪቷ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ የግልና የመንግሥት ጋዜጦች በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እየታተሙ ቢገኙም፣ ድርጅቱ አጋጠመኝ የሚለውን የወረቀት እጥረት ችግር እንዲሸከም የተፈረደበት የሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚ ብቻ መሆኑ ታውቋል፡፡ እስካሁን ድርጅቱ የመፍትሔ ዕርምጃ ብሎ ያስቀመጠውን ሐሳብ መተግበር የጀመረው በሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚ ላይ ብቻ ነው፡፡

ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሴንተር በበኩሉ ድርጅቱ የወሰደው ዕርምጃ ተገቢ አይደለም ሲል ተቃውሞታል፡፡ በማተሚያ ድርጅቱ በርካታ ጋዜጦች እየታተሙ እያሉ ድርጅቱ አጋጠመኝ ለሚለው የወረቀት እጥረት አንድ አሳታሚ ድርጅት ብቻ እንዲሸከመው ማድረግ ተገቢ አይደለም ብሏል፡፡ በመሆኑም የብርሃንና ሰላም ውሳኔ በጋዜጣው ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያስከትል አስታውቋል፡፡ ‹‹ተፈጠረ የተባለው የወረቀት እጥረት ችግር እውነተኛ ከሆነ የመንግሥት ሕትመቶችን ጨምሮ በማተሚያ ድርጅቱ የሚጠቀሙ ሁሉም የሕትመት ውጤቶች ችግሩን በጋራ ሊሸከሙት ይገባል፡፡ ሆኖም በአንድ ድርጅት ላይ ብቻ ሁሉን ነገር መጣል ተገቢ አይደለም፤›› ሲል ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽንስ ሴንተር የማተሚያ ቤቱን ዕርምጃ ተቃውሟል፡፡


በማተሚያ ድርጅቱ ከሚታተሙና ከፍተኛ ፍጆታ ካላቸው አሳታሚዎች መካከል የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ አንዱ ነው፡፡ ይህ አሳታሚ ድርጅት በየቀኑ በአማካይ ባለ18 ገጹን አዲስ ዘመንና ባለስምንት ገጹን ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣዎች ያሳትማል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ በሳምንት በአማካይ 180 ገጽ ጋዜጣዎችን ያስትማል፤ ይህም ከሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ሴንተር ቀጥሎ የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ በማተሚያ ድርጅቱ ከፍተኛ ፍጆታ ካላቸው ድርጅቶች በሁለተኛነት ያስቀምጠዋል፡፡ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሴንተር በሳምንት ሦስት ጋዜጦችን ሲያሳትም፣ በአማካይ 220 ገጾች አካባቢ በሳምንት ይጠቀማል፡፡ በመሆኑም ከኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ጋር የ40 ገጽ ልዩነት አለው፡፡ ሆኖም በሚገርም ሁኔታ ግን ለዚህ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ለሚገኝ አሳታሚ የገጽ ግደባ ደብዳቤ ከማተሚያ ቤቱ እስካሁን አልደረሰውም፡፡

ጉዳዩን አስመልክተን የማተሚያ ድርጅቱን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለን አነጋግረናቸው፣ ‹‹ሪፖርተር ጋዜጣ ከፍተኛ ፍጆታ አለው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የሚታተመው በሳምንት ሦስቴ ስለሆነ ነው ይህ ውሳኔ የተወሰነው፤›› በማለት ቢናገሩም፣ በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ ፍጆታ ያለውና ከሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚ ብዙም ልዩነት ለሌለው የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ምንም ዓይነት ደብዳቤ እንዳልተላከ አቶ ሽታሁን ገልጸዋል፡፡

ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽንስ ሴንተር ጉዳዩ እንዲታይለት በጠየቀው መሠረት ችግሩንም ሌሎች አሳታሚ ድርጅቶች እንዲጋሩት ለማድረግ እየተጠና መሆኑን የተናገሩት አቶ ሽታሁን፣ ውጤቱን በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በግምጃ ቤቱ ከሦስት ሜትሪክ ቶን በታች ወረቀት መያዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምንም እንኳን ማተሚያ ድርጅቱ የወረቀት እጥረቱን ምክንያት ባይገልጽም፣ ምንጮች ድርጅቱ ሌተር ኦፍ ክሬዲት መክፈት ባለመቻሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በግል አሳታሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡ ባለፈው ነሐሴ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የማስታወቂያ አዋጅ መሠረት የጋዜጦች የማስታወቂያ ሽፋን ከ60 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ይደነግጋል፡፡

ይህ አዋጅ በተለይ በመንግሥት በማይደጐሙና ገቢያቸውን ከማስታወቂያ የሚያገኙ ጋዜጦችን ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ መንግሥት በመጀመርያ ረቂቅ አዋጁን አዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ሲያደርግ፣ የጋዜጦች የማስታወቂያ ሽፋን ከ70 በመቶ መብለጥ የለበትም ይል ነበር፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ረቂቅ አዋጁን አዘጋጅቶ ለውይይት ባቀረበበት ወቅት፣ የጋዜጦች የማስታወቂያ ሽፋን ከ70 በመቶ መብለጥ አለበት ወይም የለበትም የሚለውን ጉዳይ እምብዛም እንደማያስጨንቀው፣ አስፈላጊ ከሆነም የማስታወቂያ ገደቡ ከነጭራሹ ሊቀር እንደሚችል ገልጾ ነበር፡፡ ሆኖም በተገላቢጦሽ አዋጁ ሲፀድቅ የጋዜጦች የማስታወቂያ ሽፋን 60 በመቶ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

በመንግሥት የሕትመት ኢንዱስትሪውን በማይደጉምበትና የማተሚያ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በጨመረበት በአሁኑ ጊዜ ላይ ማተሚያ ድርጅቱ ይባስ ብሎ የገጽ ቁጥር መገደቡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው ተብሏል፡፡

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይም ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለአሳታሚዎች ያሰራጨው ረቂቅ የኮንትራት ውል ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ ይህ ረቂቅ ውልም በሕገ መንግሥቱ የሚከለክለውን ቅድመ ምርመራ በመቃረን ማንኛውንም ሕትመት ይዘት ከመረመርኩ በኋላ ነው የማትመው የሚል ነበር፡፡ ሆኖም አሳታሚዎች ይህ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠንን መብት የሚጋፋ ነው በማለት በመቃወማቸው ማተሚያ ድርጅቱ ውሉን በዚያው አድበስብሶ አልፎታል፡፡

ማተሚያ ድርጅቱ መጋቢት 2003 ዓ.ም. ላይ የሕትመት ዋጋ ላይ 45 በመቶ በመጨመር በተለይ የግል አሳታሚዎች ላይ ያሳረፈው ጡጫ ይታወሳል፡፡

መንግሥት በአንድ በኩል ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን አራምዳለሁ እያለ በሌላ በኩል የዚህ መብት ዋነኛ ምሶሶ የሆነው የአገሪቱ የግል ፕሬስ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ አስተያየት ሰጪዎችም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የአቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ‹‹የመለስ ራዕይ ሳይበረዝ ይቀጥላል፤›› ማለታቸውን በማስታወስ፣ በአንድ አገር ሰብዓዊ መብትንና ዲሞክራሲን ለማስጠበቅ ‹‹የፕሬስ ነፃነት ሳይበረዝ መቀጠል አለበት›› በማለት ተናግረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment