Wednesday 3 October 2012

ተቃዋሚ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ሕዝብ የብቃት ማረጋገጫ ሊያሳዩ ይገባል

በአንድ አገር የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመኖሩ አንዱ ማሳያ የተለያዩ አመለካከቶችና አማራጮች በኅብረተሰቡ ውስጥ ሲንሸራሸሩ ነው፡፡ ተራ መንሸራሸር ሳይሆን በተደራጀ ሁኔታ የእኔ ሐሳብ ከዚያኛው ሐሳብ ይበልጥ ለአገርና ለሕዝብ ይጠቅማል በሚል ይዘትና ቅርፅ ሲሰራጭ ነው፡፡ በፖለቲካ ድርጅት መልክና ቅርፅ፡፡
 
‹‹እነጭር ሲል አልወድም›› ቢኖሩም፣ ባይኖሩም ሕዝቡ ግን ከዚህኛው ፓርቲ አመለካከት የሚሻለው የዚያኛው ፓርቲ አመለካከት ነው ብሎ መምረጥ መቻል አለበት፡፡ በድምፅ ብልጫ ያሸነፈው አስተሳሰብ የመንግሥት አመለካከት እንዲሆን ነው፡፡

በአገራችን በኢትዮጵያም ይህ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ሕገ መንግሥቱም ይደነግጋል፤ ይፈቅዳል፡፡ በተግባር ግን እውን ሆኖ ሊታይ አልቻለም፡፡ ገዢው ፓርቲም አለ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም አሉ፡፡ አማራጭ የሚባሉት አመለካከቶች ግን በግልጽ ሊታዩ አልቻሉም፡፡

ገዢው ፓርቲ የእኔ መንገድና አመለካከት ይህ ነው ብሎ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ሕዝብ ይውደደውም፣ አይውደደውም የገዢው ፓርቲ አመለካከት በግልጽ ተቀምጦለታል፡፡ የተቃዋሚዎች ግን አልተቀመጠም፡፡ ሕዝብ ይውደደውም፣ አይውደደውም እኛ ሥልጣን ብንይዝ ፕሮግራማችን፣ ስትራቴጂያችን፣ መስመራችን፣ ፖሊሲያችን ይህ ነው ተብሎ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አልቀረበም፡፡

በዚህ ምክንያትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቃዋሚዎችን በሚገባ ሊያውቅ፣ ሊጠይቅና ሊከተል አልቻለም፡፡ ብቃታቸውን ስለማያውቅና ስለሚጠራጠር ደግሞ ኢሕአዴግን ተክተው ኢትዮጵያን ስለመምራታቸው ሊታየው አልቻለም፡፡

ስለሆነም ዋናውና አንገብጋቢው የኢትዮጵያ የወቅቱ የፖለቲካ ጥያቄ ብቃት ያለው ተቃዋሚ ድርጅት በግልጽ፣ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ማየት ሆኗል፡፡ ስለሆነም ነው ‹‹ተቃዋሚ ድርጅቶች ሆይ እባካችሁን የብቃት ማረጋገጫችሁን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳዩ›› እያልን ያለነው፡፡ በተደጋጋሚም የምንለው፡፡ ሕዝብ ተቃዋሚዎች የብቃት ማረጋገጫ እንድታቀርቡ እየጠየቀ ነው፡፡

ሕዝብ ከተቃዋሚዎች እየጠየቀ ያለው የብቃት ማረጋገጫ ምንድን ነው?

ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በሁለት መመዘኛ ተጠናቆ የቀረበ የብቃት ማረጋገጫ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማቅረብ አለባቸው፡፡ በአንደኛው ክፍል በዓላማ፣ በፕሮግራምና በስትራቴጂ ካለው ገዥ ፓርቲ እነሱ የተሻሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ሰነድ ነው፡፡

የፖለቲካ ፕሮግራም ነድፈው በግልጽ ለሕዝብ ማቅረብ አለባቸው፡፡ አመለካከታቸውና የፖለቲካ መስመራቸው ምን እንደሆነ፣ ለኢትዮጵያ እንዴት ሊጠቅም እንደሚችል፣ ከገዢው ፓርቲ አመለካከት እንዴት የተሻለ መሆኑን ስትራቴጂያቸውን በግልጽ ሊያቀርቡ ይገባል፡፡

በእርሻ፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በፍትሕ፣ በዲፕሎማሲ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሰብዓዊ መብት፣ በፕሬስ ነፃነት፣ በሉዓላዊነትና ደኅንነት ያላቸውን አቋም በግልጽ ሲያቀርቡ ነው ገዢውን ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲን አወዳድሮ ሕዝቡ የምርጫ አቋም ሊወስድ የሚችለው፡፡

በሁለተኛው ክፍል አደረጃጀታቸውና ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ምን እንደሚመስል የሚያይበት፣ የሚሰማበትና ብሎም ፍርድ የሚሰጥበት ሰነድና ተግባር ነው፡፡

ለመሆኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች እውነት አባላት አሉዋቸው? ምን ያህል ናቸው? በውስጣቸው ዴሞክራሲያዊ አሠራር አላቸው? ምርጫ ያካሂዳሉ? የሒስና የግለሒስ፣ የግምገማና የመተቻቸት መድረክ አላቸው? ዴሞክራሲያዊ ነው? ነፃ ነው? ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውስጣቸው የአመራርና የኃላፊነት መተካካት አላቸው? ለምን ሽማግሌዎች በዙ?

ይህ በግልጽ ለሕዝብ መቅረብ አለበት፡፡ ምክንያቱም በውስጣዊ አሠራሩ ዴሞክራሲያዊና ነፃ የሆነ አካሄድ የማይከተል የፖለቲካ ድርጅት ሥልጣን ሲይዝ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ አሠራር ያሰፍናል ማለት ዘበት ነውና፡፡ ራሱ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ፓርቲ ሌላውን ዴሞክራሲያዊ አይደለም እያለ ለመውቀስ አይችልምና፡፡

ከእነዚህ መመዘኛዎች አንፃር ሲታዩ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች ደካሞች ናቸው፡፡ አመለካከታቸውም፣ ፕሮግራማቸውም፣ ስትራቴጂያቸውም፣ የፖለቲካ መስመራቸውም፣ ሥልጣን ቢይዙ ምን ሊያደርሱ እንደሚችሉም ለኢትዮጵያ ሕዝብ በእጅጉ ግልጽ አይደለም፡፡ ስለሆነም ሕዝብ ብቃት የላቸውም እያለ ነው፡፡

በተግባራዊ እንቅስቃሴያቸውም ቢሆን ሲጣሉ፣ ሲከፋፈሉና ሲወነጃጀሉ ሲያይና ሲሰማ እንጂ ምርጫ ሲያካሂዱ፣ ሲተካኩና ሲገማገሙ አይቶም ሰምቶም አያውቅም፡፡ ከዚህ አንፃርም ብቃት የላችሁም እያለ ነው፡፡ ሕዝቡ!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውጭ አገር የሚገኙና የትጥቅ ትግል እናካሂዳለን የሚሉ ተቃዋሚዎች ነን ባዮች የሚያደርጉትን ሁሉ ሕዝቡ ታዝቧል፡፡ በተለይም ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መታመምና ሕልፈት ጋር በተገናኘ እነዚህ ወገኖች ሲያደርጉት በነበረው እንቅስቃሴ ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተቃዋሚዎች ላይ ትዝብቱንና ክትትሉን እንዲያጠናክር አድርጎታል፡፡ ድርጊታቸው በርካታ ጥያቄዎችንም እንዲያነሳ ስላደረገው በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተው አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ጠንከር ያሉ መመዘኛዎችን ሊያቀርብላቸው ተገዷል፡፡

ሕዝብ ሁለቱም የተለያዩ መሆናቸው ቢያውቅም፣ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድን ተከትለው የሚንቀሳቀሱ አገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች ከእነዚያ የተለዩ መሆናቸውን ቢረዳም፣ የእነዚያኞቹ ጽንፈኛ፣ አሳፋሪና አስነዋሪ አቋምና እንቅስቃሴ በሕዝብ ውስጥ ተጠራጣሪነትን ፈጥሯል፡፡

ይህም ስለሆነ ነው ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ተከትለው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ተቃዋሚዎች የሕዝብን አመኔታና ክብር እንዲያገኙ፣ የብቃት ማረጋገጫቸውን ለሕዝብ ማቅረብ ያለባቸው፡፡ በተግባር!

አንድ ነጥብ ግልጽ እናድርግ፡፡ ተቃዋሚዎች መጠናከርና ብቃት እንዲኖረን ያልቻልነው በኢሕአዴግ ምክንያት ነው ብለው መልስ ሊሰጡ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ በእርግጥ መንግሥትም ገዢው ፓርቲም ተቃዋሚዎች እንዲጠናከሩና የፖለቲካ ሕይወት እንዲዳብር ተገቢ ሥራ አልሠሩም፤ የድርሻቸውን አልተጫወቱም፡፡ እዚህ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡

ግን! ነገር ግን! ተቃዋሚዎች የፈለጉትን ምክንያትና ሰበብ ቢያቀርቡም ፕሮግራምና ስትራቴጂ ነድፈን ለሕዝብ እንዳናቀርብ ኢሕአዴግ አደናቀፈን፣ በውስጣችን ምርጫ እንዳናካሂድ፣ መተካካት እንዳናደርግ መንግሥትና ኢሕአዴግ ከለከሉን፣ አባላት እንዳንጨምርና ግምገማ እያካሄድን እንዳንጠናከር ታፈንን ሊሉ አይችሉም፡፡ ይህ የገዛ ራሳቸውና የውስጣቸው ድክመት ነው፡፡

ይልቁንስ ተቃዋሚዎች ሆይ ድክመታችሁን አጥኑ፡፡ ችግሮችን በመጋፈጥ ተስተካክሉና የብቃት ማረጋገጫችሁን ለሕዝብ አቅርቡ፡፡ ሕዝብ ‹‹ሀቀኛ ተቃዋሚን ያየህ ወዲህ በለኝ›› እያለ ነውና፡፡


No comments:

Post a Comment